አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል አለ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት።
ዓለም አቀፍ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል ቀን “ከማጭበርበሩ ጀርባ ያለው ወጥመድ” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አባባ እየተከበረ ነው።
በዚህም ወቅትም በደቡብ ምስራቅ እስያ አካባቢ የተፈጠሩ ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ቡድኖች እየተበራከቱ እንደሚገኙ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አመልክቷል፡፡
ኢትዮጵያም ለዚህ ችግር ተጋላጭ መሆኗን የጠቀሰው ድርጅቱ ÷ ጉዳዩ ፈጣን ምላሽ የሚያስፈልገው መሆኑን አጽንኦት ሰጥቷል፡፡
የፍትሕ ሚኒስትር ዴዔታ ቸርነት ሆርዶፋ በበኩላቸው ÷ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
አዘዋዋሪዎቹ በተማሩ ወጣቶች ላይ ትኩረት በማድረግ የተሻለ የሥራ እድል እንዳለ በማስመሰልና ሕጋዊ የሚመስሉ ማስረጃዎችን በማዘጋጀት ዜጎችን እንደሚመለምሉ አብራርተዋል፡፡
ይሁን እንጂ በተለይ ወጣቶች በአውሮፕላን በሚደረግ ጉዞ ከኢትዮጵያ ከወጡ በኋላ የግዳጅ ወንጀል እንዲሰሩ ይገደዳሉ ፤ ለአካል እና ለሥነ ልቦና ጉዳትም ተጋላጭ ይሆናሉ ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ለዚህ ችግር የተጋለጡ ከ2 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉን ጠቁመው ÷ በቀጣይ ችግሩን ለመከላከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በሚልኪያስ አዱኛ

