ታላቅ የንግድ ኤክስፖና ፌስቲቫል በአዲስ ኮንቬንሽን ማዕከል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ፣ 2018፣ መጪውን 2019 አዲስ ዓመት ምክንያት በማድረግ አደይ አዲስ ዓመት ታላቅ የንግድ ኤክስፖና ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ኮንቬንሽን ማዕከል ይካሄዳል፡፡
በማስተር ፒስ ትሬዲንግ” እና “ራይት ኢቨንት” የተዘጋጀው የ2019 አዲስ አመት መቀበያ “አደይ አዲስ ዓመት ታላቅ የንግድ ኤክስፖና ፌስቲቫል በአዲስ ኮንቬሽን ሴንተር ከነሐሴ 21 ቀን እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ነው የሚካሄደው፡፡
ዝግጅቱ አዲስ አበባን እና ኢትዮጵያን በንግድ፣ በባህል፣ በቱሪዝም፣ በፈጠራ እና በዝግጅት ኢንዱስትሪ ለማስተዋወቅ፣ ለወጣቶችና ለነጋዴዎች እድል ለመፍጠር እና የአዲስ ዓመትን ደስታ በጋራ ለማክበር ነው ያለመ ነው።
ፌስቲቫሉ ሸማቹ ሕብረተሰብ ከአካባቢው ብዙም ሳይርቅ ምርትና አገልግሎት በብዛት ቀርቦለት አማርጦ በተሻለና ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸምት ያስችላል፡፡
ለዚህም አስፈላጊው ቅደም ዝግጅት የተጠናቀሰ ሲሆን÷ ነጋዴዎች፣ አስመጪዎች፣ የተለያዩ አገልግሎት አቅራቢዎችም በመመዝገብ ላይ ይገኛሉ፡፡
ኮንቬንሽን ሴንተሩ በሺዎች የሚቆጠር መኪናዎችን ማሰተናገድ የሚችል ሲሆን ÷ ፌስቲቫሉን በቀን ከ10 ሺህ በላይ ሕዝብ ሊጎበኘው ይችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አዲስ ኮንቬንሽን ሴንተር ከሚዋስናቸው የሰሚት፣ የአያት፣ የአራብሳ፣ የየካአባዶ፣ የኮተቤ ነዋሪዎችን ጨምሮ በሚልየን የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በዙሪያው ይገኛሉ፡፡
እነዚህ ነዋሪዎች ሩቅ ተጉዘው ለበዓሉ የሚያደርጉትን አድካሚ ሸመታ በማስወገድ በቅርብ ርቀት ላይ ግብይታቸውን እንዲያደርጉ የሚያስችል መሆኑ ተመራጭ ያደርገዋል፡፡
ከ200 በላይ የኢትዮጵያ አምራቾች፣ አስመጪዎች፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች፣ የፋሽንና የውበት ዘርፍ፣ የቤት ዕቃዎች፣ የምግብና መጠጥ አምራቾች፣ የቴክኖሎጂና የአገልግሎት ተቋማት ምርቶቻቸውን በቀጥታ ለሸማቾች የሚያቀርቡበት ትልቅ የንግድ መድረክ ነው።
ከንግድ እና ግብይት ባሻገር፣ “አደይ የአዲስ ዓመት ታላቅ የንግድ ኤክስፖ እና ፌስቲቫል” በመዲናዋ ለሚገኙ ቤተሰቦች እና ለሚመጡ የዳያስፖራ አባላት የባህል መሰባሰቢያ ማዕከል ሆኖ ለማገልገል አቅዷል፡፡
ፌስቲቫሉ በ15ቱ ቀናት ውስጥ15 የሙዚቃ ድግሶች ከአንጋፋ እና ተወዳጅ አርቲስቶች ጋር የሚቀርብ ሲሆን ÷ በፌስቲቫሉ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ኮንሰርትም ከ8 ሺህ በላይ ታዳሚዎች ይጠበቃሉ።
በተጨማሪም ባለተሰጥኦ ዲዛይነሮች የሚያቀርቡትን የፋሽን ትርኢት፣ የስታንድአፕ ኮሜዲ፣ የዳንስ እና ልዩ ልዩ ትርዒቶችን አካትቶ ይቀርባል።
ፌስቲቫሉ ከሚያቀርባቸው ማህበራዊ ቁምነገሮች መካከል ሰፋ ያለ የመጻህፍት አውደ ርዕይ፣ የመጻህፍት ልገሳ እና የጠፉ መጻህፍት ሽያጭ ይገኙበታል። እንዲሁም በርካታ የበጎ አድራጎት ሥራዎች የሚከናወኑበት መድረክ በመሆን ያገለግላል።

