አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ለእርሻና ለመስኖ ልማት የሚያገለግል የውሃ አስተዳደር ሥርዓትን ማጠናከር አስፈላጊ ነው አለ።
በምስራቅና በመካከለኛው የፓሲፊክ ውቅያኖስ የባሕር ወለል ሙቀት መጨመር ኤልኒኖን ሊያስከትል እንደሚችልና በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የክረምት ዝናብ ቀደም ብሎ ሊቋረጥ እንደሚችል አመልክቷል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ ባለፈው የሰኔ ወር በምዕራብ፣ በሰሜን እና ሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች እስከ 100 ሚሊሜትር የሚደርስ ከፍተኛ የዝናብ መጠን ተመዝግቧል።
ይህም ለማሳ ዝግጅት እና ለአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ በክረምቱ ወቅት የሚኖረውን የዝናብ ሁኔታ በሳይንሳዊ ትንተና በመመርኮዝ ቀድሞ በማሳወቅ በግብርና፣ በውሃ ሀብት፣ በአካባቢ ጥበቃና በአደጋ ስጋት ቅነሳ ሥራዎች ላይ ጠቃሚ መረጃ እያቀረበ መሆኑን አመልክተዋል።
በትግራይ፣ በመካከለኛ እና በምዕራብ አማራ አንዳንድ ዞኖች መደበኛ ወይም ከመደበኛ በታች የሆነ የዝናብ መጠን ሊመዘገብ እንደሚችል ትንበያው ያሳያል።
በአንጻሩ በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በምዕራብ ኦሮሚያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና በጋምቤላ ክልሎች በአብዛኛው መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠን እንደሚጠበቅ አብራርተዋል።
በቀጣዩ ነሐሴ ወር በምስራቅና በመካከለኛው የፓሲፊክ ውቅያኖስ የባሕር ወለል ሙቀት መጨመር የኤልኒኖ ክስተትን የማስከተል ዕድል እንዳለው አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች እንደሚያመለክቱ ገልጸዋል።
በዚህም ምክንያት በአንዳንድ የምስራቅና የሰሜን የሀገሪቱ አካባቢዎች የክረምት ዝናብ ከተለመደው ቀደም ብሎ የመቋረጥ እድል እንዳለ ጠቁመዋል።
የግብርናው ዘርፍ ከሚከሰቱ የአየር ጸባይ ተጽዕኖዎች ለመጠበቅ የዝናብ ሁኔታን የሚመጥኑ ሰብሎችን መጠቀም፣ በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ሰብሎችን ማምረትና ድርቅ መቋቋም የሚችሉ ዘሮችን መዝራት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም የውሃ ማሰባሰብና የውሃ ማቆር ሥራዎችን በማጠናከር ለእርሻና ለመስኖ ልማት የሚያገለግል የውሃ አስተዳደር ሥርዓትን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና የግብርና ባለሙያዎች የአየር ሁኔታ ትንበያ መረጃዎችን መሰረት በማድረግ ለአምራቹ ህብረተሰብ አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በዮናስ ጌትነት

