አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ሀብታቸውን በአግባቡ አሟጠው በመጠቀም ልማት ለማስመዝገብ ትልቅ ተግዳሮት ይገጥማቸዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ አስፈላጊ የሆኑ ምርቶችንና ጥሬ ዕቃዎችን ወደ ውጭ ለመላክም ይሁን ወደ ሀገር ውስጥ የማስገባት ፍላጎታቸው በሌሎች ሀገራት ይሁንታና በጎ ፈቃድ ላይ ይወድቃሉ፡፡
ኢትዮጵያም ባለፉት 30 ዓመታት ይህ ዕጣ ፈንታ ገጥሟታል፡፡ ካላት የተፈጥሮ ሃብት እና የሕዝብ ቁጥር ብዛት አንጻር በፍጥነት እያደገ ያለውን ኢኮኖሚዋን የሚደግፍና የሚያጠናክር የባሕር በር አለመኖር በምትፈልገው ልክ እንዳትሰራ እንቅፋት ሆኖባት ቆይቷል፡፡
ሀገራችን በዓለም ትልቅ የሕዝብ ቁጥር ኖሯቸው የባሕር በር ከሌላቸው ሀገራት በአንደኝነት ትመራለች፡፡ ኡጋንዳ፣ ኡዝቤኪስታን፣ አፍጋኒስታንና ኔፓል ደግሞ በቅደም ተከተል ከ2ኛ እስከ 5ኛ ደረጃ ያለውን ቦታ ይዘዋል፡፡
የአራቱ ሀገራት ጠቅላላ የሕዝብ ቁጥር ተደምሮ 157 ሚሊየን የሚደርስ ሲሆን ÷ ኢትዮጵያ ብቻዋን ከ130 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ይዛ ከባሕር በር እንድትገለል ተደርጋለች፡፡
ኢትዮጵያ ከአምስቱ ብዙ የሕዝብ ቁጥር ካላቸው ሀገራት ከባሕር ጠረፍ ያላት ርቀት ስናይ እጅግ በጣም አጭሩ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ለምሳሌ አፍጋኒስታን ከባሕር ጠረፍ በ457፣ ኡጋንዳ በ480፣ ኔፓል በ690፣ ኡዝቤኪስታን በ900 ኪሎ ሜትር ሲርቁ÷ ኢትዮጵያ ግን ከቀይ ባሕር ጠረፍ 60 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው የምትርቀው፡፡
ከ130 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ በዚህ ቅርብ ርቀት ሆና የባሕር በር እንድታጣ የተደረገበት ታሪካዊ ሸፍጥ አስገራሚና የውስጥ ተባባሪዎችም ትውልድ ይቅር የማይለው በደል የፈጸሙበት ሁነት ነው፡፡
በታሪክ የባሕር በር ያልነበራቸው እና በመቶዎች ኪሎ ሜትር የሚርቁ በርካታ ሀገራት በተለያዩ መንገዶች የባሕር በር ማግኝት ችለዋል፡፡ የባሕር በር ጥያቄዎች በታሪክ መልስ ያገኙባቸውን መንገዶች ማወቅ ትምህርት ስለሚሆን ማንሳት ተገቢ ይሆናል ፡፡ ለዚህም ዮርዳኖስ፣ ቦሊቪያ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን እንደምሳሌ እንመልከት፡፡
ዮርዳኖስ በጣም ቅርብ ከሆነ የባሕር ጠረፍ በ300 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኝ የባሕር በር ያልነበራት ሀገር ስትሆን ፤ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር ተደራድራ በመሬት ልውውጥ የባሕር በር ለማግኘት ችላለች፡፡
በድርድሩ መሰረት ሳዑዲ ለዮርዳኖስ በአቃባ ባሕረ ገብ በኩል18 ኪሎ ሜትር ያህል ርዝመት ያለው የባሕር ጠረፍ የሰጠቻት ሲሆን÷ ዮርዳኖስ በምላሹ 6 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር መሬት ለሳዑዲ ዓረቢያ ሰጥታለች፡፡
ሁለተኛዋ የባሕር በር በስምምነት ያገኘችው ሀገር ቦሊቪያ ስትሆን ÷ ሀገሪቱ በጣም ከሚቀርባት የባሕር ጠረፍ በ160 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡
ቦሊቪያ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የባሕር ዳርቻዋ በቺሊ ከተወሰደባት በኋላ በፈረንጆቹ 1992 ከፔሩ ጋር ቦሊቪያማር በተሰኘ ስምምነት የ99 ዓመት ሊዝ የባሕር በርና ዳርቻ ማግኘት ችላለች፡፡
በባሕር በሩ እና ዳርቻው ቦሊቪያ ነጻ የንግድ ቀጣና፣ የጉምሩክ እንዲሁም የባሕር ኃይሏን ማዕከል ገንብታ እየተጠቀመችበት ትገኛለች፡፡
ምንም እንኳን የባሕር በር እንዲኖራት የተደራደሩት ቅኝ ገዢዎች ቢሆኑም የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ታሪክ ትምህርት የሚሆን ነው፡፡
አውሮፓውያን አፍሪካን የተቀራመቱበት በታሪክ የበርሊን ኮንፈረን እየተባለ የሚጠራው ሁነት ወቅት የቤልጂዬሙ ንጉስ ሊዎፖልድ ዳግማዊ እንደ ግል ንብረቱ በቅኝ ግዛት ለያዛት ኮንጎ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት ተከራክሮ ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ የሚደርስ ጠባብ ኮሪዶር እንዲኖራት አስችሏል፡፡
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በመሰረታዊነት በፖለቲካ አሻጥር በሕገ ወጥ መንገድ የተወሰደባትን ንብረት በሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ የማስመለስ ጉዳይ ነው፡፡
ይህ ሕጋዊ፣ ፍትሃዊና የሕልውና ጥያቄ መልስ እስኪያገኝ ድረስም ሁሉም ኢትዮጵያዊ እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመቆም የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል፡፡
በቴዎድሮስ ሳህለ

