ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ያጣነውን የባህር በር ለመመለስ ጊዜው ደርሷል::
የኤርትራን መገንጠል ተከትሎ በተሰጠው የፖለቲካ ውሳኔ፣ ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታጣ ቀጥተኛና የመጨረሻው ምክንያት ሆኗል፡፡
ይህ ታሪካዊ ክስተት ሀገሪቱን በዓለም ትልቁን የህዝብ ቁጥር ይዛ የየብስ ዝጓ ሀገር አድርጓታል።
የባህር በር ለአንድ ሀገር የኢኮኖሚ የደም ሥር፣ የሉዓላዊነት መገለጫ እና የጂኦፖለቲካዊ ተጽዕኖ መሣሪያ እንደሆነ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ ለዘመናት በቀይ ባህር አካባቢ የራሷ የወደብ ባለቤት የነበረች ቢሆንም፣ በተፈጠረው ስህተት የባህር በር አልባ ሀገር ሆናለች።
ኢትዮጵያ የባህር በሯን ያጣችው የወደብን ዘላቂ ጥቅም ባለመረዳትና ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ብሔራዊ የደህንነት ስትራቴጂ ባለመኖሩ ነው።
የባህር በር ማጣት ሀገሪቱን ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ኪሳራ ዳርጓታል።
ለሌላ የልማት ሥራ ሊውል የሚችል በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በየዓመቱ ለጅቡቲ የወደብ ክፍያ ይወጣል፡፡
ወደብ አልባ መሆን ደግሞ በዓለም አቀፍ ንግድ ላይ ጥገኝነትን ስለሚፈጥር፣ ኢትዮጵያ በጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች ወቅት በቀላሉ እንድትጎዳ አድርጓታል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችው በሁለት ዋና ዋና ምዕራፎች ነው፡፡
በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማጠናቀቂያ ላይ የጣሊያ ቅኝ ገዥዎች የባህር ዳርቻውን በመውሰዳቸው የመጀመሪያው ታሪካዊ ስብራት ተፈጠረ።
ሁለተኛው ግን በታሪክ አጋጣሚ የተገኘውን ዕድል ያመከነ ነው፡፡
1983 ዓ.ም የደርግ ሥርዓት መውደቅን ተከትሎ፣ 1985 ዓ.ም በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ኤርትራ ሙሉ በሙሉ ስትገነጠል፣ ኢትዮጵያ የነበራትን የወደብ በር በአንድ ጀምበር እንድታጣ ተደርጓል፡፡
ለዚህ ታሪካዊ ኪሳራ የወቅቱ የኢሕአዴግ የሽግግር መንግሥት ተጠያቂ ነው፡፡
የኤርትራን መገንጠል ሲቀበል የኢትዮጵያን ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅም ከግምት ማስገባት ነበረበት፡፡
ይህንን ባለማድረጉ፣ የኢትዮጵያን የባህር በርና የወደብ ባለቤትነት መብት ያለምንም ቅድመ ሁኔታና የሕግ ክርክር ለኤርትራ አሳልፎ ሰጥቷል፡፡
በተለይም የአሰብ ወደብን ታሪካዊ፣ ሕጋዊና ስነ-ህዝባዊ መሰረት ግምት ውስጥ በማስገባት ለኢትዮጵያ አማራጭ የባህር በር ለማስከበር አለመሟገቱ ታሪካዊ ስህተት ነበር።
የነበረውን ድክመት ከግምት በማስገባት የውጭ ኃይሎችም የውስጥ ተላላኪዎችን በመጠቀም ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር እንድትርቅ አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያን ወደብ አልባ ለማድረግ ለባንዳዎች ብዙ ገንዘብ ከፍለዋል፤ የዲፕሎማሲ ጫናም አሳድረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዋናነት የባህር በር ያጣችው በ1983 ዓ.ም በነበረው የውስጥ የፖለቲካ አመራሮች ስትራቴጂካዊ ስህተት እና የረጅም ጊዜ ብሔራዊ ጥቅም አርቆ አሳቢነት በመጥፋቱ ነው።
ይህ የታሪክ ኪሳራ ዛሬም ድረስ የሀገሪቱን ዕድገትና ሰላም እየተፈታተነ ይገኛል።
አሁን ያንን ስህተት ለማረምና ለቀጣዩ ትውልድ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማውረስ የመደመር መንግሥት እየተሰራ ነው፡፡
በሰላማዊ መንገድና በጋራ የመልማት መርህ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመደራደር የባህር በር ጥያቄ የህልውና ጉዳይ ሆኗል፡፡
የመደመር መንግሥት ያነሳውን የባህር በር ጥያቄ ማሳካት የሁላችንም ድርሻ ሲሆን፣ ጊዜውም አሁን ነው፡፡

