Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአየር ንብረት ለውጥ መዘዝ በአውሮፓ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአየር ንብረት ለውጥ በመላው አውሮፓ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ እያስከተለ ይገኛል፡፡

በአህጉሪቱ በተለይም ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ቤልጂዬም፣ ኔዘርላንድስ እና ስፔን በሰኔ ወር መጨረሻ አካባቢ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻቸው በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት ለሕልፈት ተዳርገዋል፡፡

በጀርመን ብቻ በዓመቱ እስከ ሐምሌ ወር አጋማሽ ከከፍተኛ ሙቀት መጨመር ጋር በተያያዘ ከ9 ሺህ 800 በላይ ዜጎቿ ሕይወታቸው አልፏል፡፡

ይህም በአስርት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከተከሰተው ሞት ጠቅላላ ድምር የሚበልጥ መሆኑን ስዊድን ሄራልድ የተሰኘው የመረጃ ምንጭ ዘግቧል፡፡

ከሟቾቹ ውስጥ 5 ሺህ 100 ያህሉ ሕይወታቸው ያለፈው በፈረንጆቹ 2026 ከሰኔ 22 እስከ 28 ባሉት ቀናት መሆኑ ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ ምን ያህል አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን የሚያሳይ ነው፡፡

በአውሮፓ ህብረት ሀገራት ውስጥ ብቻ በተጠቀሱት ቀናት 10 ሺህ ሰዎች በከፍተኛ ሙቀት መጨመር ምክንያት መሞታቸውን ሬውተርስ በዘገባው አስነብቧል፡፡ ብዙዎቹ ሟቾች ደግሞ ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ ነው፡፡

በሰኔ ወር በአጠቃላይ የፈረንሳይ 2 ሺህ 25፣ ቤልጂዬም 1 ሺህ 222፣ ስፔን 812 እና የኔዘርላንድስ 480 ዜጎች ከከፍተኛ ሙቀት ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው አልፏል፡፡

በእንግሊዝ እና ዌልስ ደግሞ በግንቦትና ሰኔ ወር በአጠቃላይ 2 ሺህ 700 የሚሆኑ ዜጎች ሕይወታቸው ማለፉን ዘገባዎች ያመላክታሉ፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ በየዓመቱ ከፍተኛ ሰብዓዊና ሥነ ምሕዳራዊ አደጋ እየፈጠረ ቢሆንም ሀገራት በችግሩ ላይ ቁርጠኛ ተግባራዊ ርምጃ ለመውሰድ ግን ዳተኝነት እያሳዩ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመታገል ባለፉት ሰባት ዓመታት ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች በመትከል የደን ሽፋኗ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር እየሰራች ነው፡፡

ከዚህ ባለፈም የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዲሻሻል በከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች፡፡

በቴዎድሮስ ሳህለ

Exit mobile version