Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የምክክር ጉባኤው አሳታፊና አካታችነት አዲስ የጋራ መግባባት የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የምክክር ጉባኤ በተመካካሪዎች መካከል የመደማመጥና የጋራ መግባባት መንፈስን በማጠናከር በተሻለ አሳታፊነት እየተካሄደ ነው አሉ የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀመንበርና ተመካካሪ አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ።
አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ÷ ምክክር ከአጀንዳ ማሰባሰብና ከተሳታፊዎች ልየታ ሂደት ጀምሮ አሳታፊነትንና አካታችነትን በተግባር በማረጋገጥ ውጤታማ ሥራ መሰራቱን አንስተዋል።
የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው አሳታፊና አካታችነት ለኢትዮጵያ አዲስ የጋራ መግባባት የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀ ነው ብለዋል፡፡
የምክክር ሂደቱ አሳታፊ፣ አካታችና ነፃ ሆኖ መካሄዱ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ሀገራዊ መግባባትና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን ገልጸዋል።
ከተመካካሪዎቹ መካከል ክብነሽ ኢዶሳ እንደተናገሩት÷ ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ዕድል ሲሆን፣ ወደ አዲስ የመግባባትና የአብሮነት ምዕራፍ የሚያሸጋግር ሂደት ነው።
የምክክር ሂደቱ አካታችና አሳታፊ መሆኑን ጠቁመው፤ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባትና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚያግዙ ገንቢ ሀሳቦች በስፋት እየቀረቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ተመካካሪ ደማይ ኮክ በኩላቸው÷ ምክክሩ ከተጀመረበት ዕለት አንስቶ ለሀገር በሚበጅ መልኩ በስኬት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
ተመካካሪዎች በንቃት እየተሳተፉ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅና ሰፊ ውይይቶችን እያካሄዱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ሌላኛው ተመካካሪ ሐብታሙ በቃሞ ፤ የምክክር ጉባኤው እጅግ አሳታፊ፣ አካታችና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንፈስ እየተካሄደ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄድ ይገኛል።
በጉባኤው በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ 4 ሺህ ተመካካሪዎች በመሰባሰብ በስምንት ዐበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት እየተመካከሩ ይገኛሉ።
Exit mobile version