አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጉምሩክ ኮሚሽን ከሐምሌ 16 እስከ 22 ቀን 2018 ዓ.ም በተደረገ ክትትል ከ704 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተይዘዋል አለ።
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ የተያዙት በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረገው የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በጥቆማ እና በበረራ እንደሆነ ተገልጿል።
661 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር የገቢ እና 43 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር የወጪ ኮንትሮባንድ እቃዎች የተያዙ መሆኑን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ በአጠቃላይ 704 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው እቃዎች መያዛቸውን አመልክቷል።
የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 34 ተጠርጣሪዎች እና 14 ተሽከርካሪዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቁሟል።
በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አዳዲስ እና ልባሽ ጨርቆች፣ ቡና፣ ጥራጥሬ፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫ፣ የቁም እንስሳት፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ መድኃኒት እና የውጭ ሀገር ገንዘቦችን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶች ይገኙበታል።
በቁጥጥር ስራው አዋሽ፣ አዲስ አበባ ኤርፖርት እና ጅግጅጋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በቅደም ተከተላቸውም 261 ሚሊየን፣ 111 ሚሊየን እና 90 ሚሊየን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎችን ይዘዋል ሲል ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

