አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክክሩ ወደ ጦርነት በወሰዱን አጀንዳዎች ላይ ተነጋግሮ ሰላምን ማምጣት የሚያስችል በመሆኑ ሕዝቡ በትልቅ ተስፋ እየጠበቀው ነው አሉ የሀገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም የተከፈተው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አሁናዊ ሂደትን በተመለከተ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በሀገር ውስጥም በውጭም ያሉ ኢትዮጵያውያን ሰላም እንዲረጋገጥና መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው በምክክሩ ላይ ትልቅ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ምክክሩ ለዘመናት ወደ ጭቅጭቅና ወደ ጦርነት በወሰዱን አጀንዳዎች ላይ በመነጋገርና አቅጣጫ በማስቀመጥ ወደ ሰላም እንድንመጣ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
ተመካካሪዎች የተለያየ ጽንፍ የያዙና የሚጋጩ ሀሳቦችን ይዘው ቢመጡም ወደ መሃል ለመምጣት የሚያደርጉት ጥረት ለምክክሩ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል ነው ያሉት፡፡
ወደ መሃል መምጣት ሀገርን የማስቀደም ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ከራሳቸው ጥያቄዎች ባሻገር በጋራ የሚጠቅሙ ጥያቄዎችን ማንሳት መጀመራቸውን አስረድተዋል፡፡
ይህም በቀጣይ በሚደረገው ዋናው ጉባኤ ላይ እየዳበረ ሀገርን ባስቀደመ መንፈስ ምክክሩ ይበልጥ እየተጠናከረ እንደሚሄድ ነው የገለጹት፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ

