የኢትዮጵያ የባህር በር የባለቤትነት ጥያቄ የፖለቲካ ፍላጎት ሳይሆን የታሪክ፣ የህግ፣ የፍትሃዊነት እና የህልውና ጥያቄ ነው።
በአሁኑ ወቅት ከ130 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ፣ በዓለማችን ላይ የባህር በር የሌላት ትልቋ ሀገር ናት።
ይህ እውነታ ሀገሪቱ በኢኮኖሚ፣ በጂኦፖለቲካ እና በደህንነት ረገድ ከፍተኛ ዋጋ እንድትከፍል አስገድዷታል።
በመሆኑም የባህር በር የማግኘት ጥያቄዋን ሙሉ በሙሉ ህጋዊ እና ፍትሃዊ ያደርገዋል።
የኢትዮጵያ ጥያቄ ከዓለም አቀፍ ህጎች እና ስምምነቶች ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጣጣም ነው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የባህር ህግ አንቀጽ 125፣ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ወደ ባህር የመድረስ እና የመጠቀም መብት እንዳላቸው በግልጽ ይደነግጋል።
ህጉ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ከባህር ዳርቻ ሀገራት ጋር በሚያደርጉት ስምምነት መሰረት ያለምንም አላስፈላጊ ጫና በትራንዚት ነጻነት የንግድ ቁሳቁሶችን እንዲያጓጉዙ ይፈቅዳል።
ኢትዮጵያ ጥያቄውን የምታነሳው በዓለም አቀፍ ህግ በተደነገገው የስምምነት እና የዲፕሎማሲ መንገድ እንጂ በሀይል ባለመሆኑ ህጋዊነቱን ይበልጥ ያጠናክረዋል።
በዚሁ መሰረት አንድን ሀገር ያለባህር በር አፍኖ ማቆየት የመልማት መብትን እንደመንፈግ ይቆጠራል፡፡
ከ130 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የራሱን ታሪካዊ የባህር በር ተነፍጎ፣ በአንድ የጎረቤት ሀገር ወደብ ኪራይ ላይ ብቻ ጥገኛ እንዲሆን መደረጉ አግባብ አይደለም፡፡
ይህ በመፈጠሩም ኢትዮጵያን ለከፍተኛ የሎጂስቲክስ ወጪ፣ ለዋጋ ንረት እና ለደህንነት ስጋት ዳርጓታል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የዘላቂ ልማት ግቦች ማንኛውንም ሀገር ወደ ኋላ አለማስቀረትን ያነገቡ ናቸው።
ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘቷ የህዝቧን የመልማትና የብልጽግና መብት የሚያረጋግጥ ፍትሃዊ ጥያቄ ነው።
ኢትዮጵያ ታሪካዊ የባህር በር የባለቤትነት መብት አላት፡፡
ቀደምት የአክሱም ስልጣኔን ጨምሮ እስከ ኤርትራ መገንጠል፣ ድረስ የራሷ ወደቦች የነበራት ጥንታዊት የባህር ሀገር መሆኗ የታሪክ እውነታ ነው።
የኢትዮጵያ ጥያቄ የሌሎችን ሉዓላዊነት የመጋፋት ፍላጎት የለውም።
ይልቁንም በጋራ ተጠቃሚነትና በሰጥቶ መቀበል መርህ የጋራ ቀጣናዊ ብልጽግናን መፍጠር ላይ ያተኮረ ነው።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የክብር ወይም የትርፍ ጉዳይ ሳይሆን የ130 ሚሊዮን ህዝብ የህልውና እና የፍትህ ጥያቄ ነው።
ጥያቄው በዓለም አቀፍ የባህር ህግ የተደገፈ ህጋዊ፣ የህዝቧን እድገት የሚያረጋግጥ ፍትሃዊ እና የቀጣናውን ሀገራት በጋራ የመልማት መርህ የሚያረጋግጥ ነው፡፡

