አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያዊያን ዘንድ አለመግባባትና ግጭቶች ሲፈጠሩ እንደየ ማህበረሰቡ አኗኗርና ልማድ እርቀ ሰላም እንዲወርድ የሚያደርጉ የካበቱ የግጭት መፍቻ ጥበቦች አሉ፡፡
በሸካቾዎች ምድር ግጭትና ቅያሜ፣ ጥላቻና ቂም ቦታ የላቸውም። ለግጭት የሚዳርግ ልዩነት ቢፈጠር እንኳ ችግሩ ውሎ አያድርም።
ቅራኔና ቂም ለትውልድ እንዳይሻገር፣ ከበድ ያለና የቆየ ጸብ ተከስቶም ከሆነ ፍትህ እንዲሰፍን፣ ሸካቾዎች ግጭትን የሚያበርዱበት፣ ልዩነትን የሚፈቱበት፣ ቅራኔን በይቅርታ ሽረው ሰላም የሚያወርዱበት ድንቅ የሆነ ሀገር በቀል ጥበብ አላቸው።
ይህ ግጭት የሚፈቱበት ጥበብ ሾቲዮ ይባላል። እነሱ ጸብና ቅያሜን እየሻሩ ሰላምና ፍቅርን እየዘሩ አያሌ ዘመን የኖሩት በሾቲዮ ነው።
በሾቲዮ ስርዓት ግጭቶችን የሚፈቱበት መንገድ እንደተከሰተው የግጭት አይነት ይለያያል የተከሰተው ግጭት ሳይታሰብ ድንገት የተፈጠረና ቀለል ያለ ከሆነ ወዲያው በሀገር ሽማግሌዎች ሽምግል ይፈታል።
ሸካቾዎች ‘ግጭት ውሎ አድሮ ወደ ሌላ ቅያሜ መሻገር የለበትም’ ብለው ያምናሉ ህዝቡ ለማህበረሰቡ፣ ለእሴቶችና ለህገ ልቦና የሚገዛ ነውና በሸካቾዎች መንደር ከፍ ያለ ግጭት የመከሰት ዕድሉ ዝቅተኛ ነው።
በተለይ ደም መቃባት በባህላቸው ነውር ነው፤ ነገር ግን አይበለውና ደም አፋሳሽ ግጭት ቢከሰት ጉዳዩ ከበድ ያለ በመሆኑ የሚዳኘው በጎሳ መሪው ፊት ነው።
በሾቲዮ ግጭት አፈታት ስርዓት ሸካቾዎች በአስታራቂ ሽማግሌዎች ቅቡልነት ጉዳይ አይደራደሩም። ለዳኝነት አይመጥንም ተብሎ የሚታሰብ ሽማግሌ ግጭት ለመፍታት አይቀመጥም፡፡
በህብረተሰቡ ተሰሚነት ያላቸውና የተፈጠረውን ችግር መርምሮ የማውጣት ብልሃት ያላቸው ብቻ ያስታርቃሉ። ልዩነትን በማስተዋል ይፈታሉ።
ሸካቾዎች ሲታረቁ ከልባቸው ስለሆነ አንዴ እርቅ ከወረደ በኋላ ቂም ይዞ መኖር አይታሰብም። በዳይና ተበዳይ ፍጹም በሆነ ይቅርታ ሰላም ያወርዳሉ ይህ ከህዝብ በተመረጡ ተቀባይነት ባላቸው ተወካዮች የዘመናት ቅራኔዎችንና ልዩነቶች ይታከማሉ፡
በግጭት አፈታት ሂደት ሸካቾዎች በውይይት ማመንን በማስቀደም ሲሟገቱም በምክንያት በመሆኑ በመጨረሻ አሸናፊ የሚሆነው እውነት ነው።
ያኔ በዳይም ሆነ ተበዳይ የሀገር ሽማግሌዎች ወይም የጎሳ መሪውን ውሳኔ ያከብራል። ውሳኔን አለማክበር ወይም አለመቀበል ከባህል እንደማፈንገጥ ይቆጠራል።
ፍርድ እንዳይዛባ የሀገር ሽማግሌዎች ወይም የጎሳ መሪው ይጠነቀቃሉ። ለበዳይም ተበደልኩ ላለም ጆሯቸውንና ልባቸውን ሰጥተው ያደምጣሉ። እውነትን በጥልቀት ይፈትሻሉ። ሀቅን ከተደበቀችበት ለማውጣት አይታክቱም። ይህ ሁለቱንም ወገኖች ያለአድሎ የማድመጥና እውነትን የመፈለግ ብልሃት በልምድ የዳበረ የማህበረሰብ እውቀት ነው፡፡
በሸካቾዎች ግጭት መፍቻ መንገድ ብዙዎች ፍትህ አግኝተው በይቅርታ እርቅ አውርደው በፍቅር መኖር ችለዋል። ለዓመታት ተዳፍነው የቆዩ ቁርሾዎች በሀገር ሽማግሌዎች የእርቅ ጥበብ ረመጥ ላይሆኑ ዛሬም ድረስ ፍትህ ሲፈልጉ እምነት በሚጥሉበት በሾቲዮ ስርዓት ይዳኛሉ፡፡
ይህ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት በዘመናዊ የፍትህ ተቋማት ታግዞ ዳግም ተደራጅቶ ስራ ከጀመረበት ከመስከረም 2017 ዓ.ም ጀምሮ ከ58 ሚሊየን ብር በላይ ክርክር ውሳኔ አግኝቷል ከ7 ሺህ በላይ ቅራኔዎች በሽምግልና ተፈተዋል።
ቅራኔዎችን በምክክር በመፍታት የጸናች ሀገር ለመሆን እየመከረች ላለችው ኢትዮጵያ ከሸካቾዎች ግጭት መፍቻ ሾቲዮ የሚቀሰመው እምቅ ጥበብ ሌላው ሀገር በቀል ዕውቀት ነው።
በተስፋየ ምሬሳ

