Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከለውጡ በፊት ከአማራ ፖለቲከኞች ጋር ትርክትን በማደስና ግድግዳ በማፍረስ ጉዳይ እንመክር ነበር – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከለውጡ በፊት ከአማራ ፖለቲከኞች ጋር ትርክትን በማደስና ግድግዳ በማፍረስ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ውይይቶች ይደረጉ ነበር አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ጋር በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸው እንዳብራሩት÷ በ2003 ዓ.ም ክረምት ከተካሄደው የከፍተኛ አመራሮች ስልጠና ጀምሮ ሲከወኑ የነበሩት ውይይቶች በሶስት ዋና ዋና አንጓዎች የተከፈሉ ነበሩ።
በውይይቶቹም መገንባት የሚፈለገው ሀገር፣ አሁን ላይ ያለው እውነታ እንዲሁም በወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ያለውን ምልከታ ያካተቱ ሀሳቦች ይነሱ እንደነበር ነው ያስታወሱት፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጵያን የመገንባት መሰረት፣ የታሪክ አረዳድ፣ ሕልምና ትልም በስፋት ይተነተን እንደነበር አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩ ብዙ ርቀት የማይጓዙና ያልተቀደሱ ጋብቻዎች እንዲህ አይነት ጥልቅ መዳረሻዎች የሚጎድሏቸው መሆኑን አስረድተዋል።
ከነዚህ ውይይቶች በኋላ የኦሮማራ እንቅስቃሴ መደረጉንና የለውጥ እንቅስቃሴው እንደ በልግ ዝናብ በፍጥነት መምጣቱን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ለዚህ ፈጣን የለውጥ እንቅስቃሴ መነሻ እርሾው እነዚያ ቀደም ሲል የተደረጉ ውይይቶች እንደነበሩ ተናግረዋል።
በወቅቱ በጎንደር በተካሄደ ሰልፍ “የኦሮሞ ደም የእኔም ደም ነው!” የሚል መልዕክት መተላለፉን አውስተው÷ ይህም ድርጊት ከመፈክር ያለፈ ትልቅ ትርጉም የነበረው መሆኑን ገልጸዋል።
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረው ከሕዝቡ ጋር መምከራቸውንና ውይይቶችን ማድረጋቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ በነዚህም መድረኮች የሕዝቡን እውነተኛ ፍላጎትና ሀሳቦች መረዳት መቻላቸውን አብራርተዋል።
እነዚህ ሁሉ አበይት ውይይቶችና የሕዝብ ግንኙነቶች አሁን ላይ ኢትዮጵያ ለምትመራበት “መደመር” ለተሰኘው ሀገራዊ ፍልስፍና መወለድ ዋና ምክንያት መሆናቸውን አንስተዋል።

Exit mobile version