Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ምክክሩ ለሀገራዊ ልማት መሰረት የሚጥል ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የሺህ ዓመታት የታሪክ ባለቤት፣ የበርካታ ቋንቋዎች፣ ባሕሎች፣ እምነቶችና ማንነቶች መኖሪያ ሀገር ናት።
ይህ የብዝሃ ማንነት በአግባቡ ከተያዘና ከተመራ ለሀገር ጥንካሬና ልማት ወሳኝ ሀብት መሆኑ ይታመናል፡፡
ብዝሃ ማንነት የልዩነትና የአለመግባባት ምንጭ ሊሆን ስለሚችል ልዩነቶችን በግጭት ሳይሆን፤ በሰላማዊ መንገድ በውይይት በምክክር መፍታት የስልጣኔ መገለጫ ነው፡፡
የተለያየ ማንነትና ፍላጎት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ፍላጎታቸውን፣ ልዩነታቸውን፣ ጥያቄዎቻቸውን በሰከነና የሌሎችን ጥያቄዎች እንዲሁም ሃሳቦች ባከበረ መልኩ የጋራ መፍትሔ ለመፍጠር የሚቻለው ደግሞ በሀገራዊ ምክክር ነው።
የምክክር መድረኩ ከአሳታፊነት፣ ከውክልና፣ ከመወያያ ርዕሰ ጉዳዮች እና ሃሳብን በነጻነት ከመግለፅ ረገድ ሂደቱ የተዋጣለት በመሆኑ ውጤቱም አስተማማኝ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
ብዝሃ ማንነት ባለበት እንደ ኢትዮጵያ ያለ ሀገር በርካታ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የታሪክ ውክልና የመሳሰሉ በርካታ ጥያቄዎች እና ፍላጎቶች እንደሚኖሩ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
ከሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ተሳታፊዎች የሀገራቸውን ወሳኝ ጉዳዮች በግልጽነትና በኃላፊነት በመወያየት፣ ልዩነቶቻቸውን በመደማመጥ እና የጋራ መፍትሔ ለመፈለግ መቀመጣቸው ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ያሏቸውን ጥያቄዎች፣ ፍላጎቶች፣ ቅሬታዎች በሰለጠነ መንገድ መወያየት ዘላቂ ሰላምን ያመጣል፡፡
ሁሉም አካላት ጥያቄዎቻቸውን አቅርበው የጋራ መፍትሄ ላይ የመድረሱ ሂደት ዘላቂ ሰላምን ከማምጣት ባሻገር በሌሎች የልማት ጥያቄዎች ዙሪያም በአንድነት እና በትብብር የመስራት ተግባራዊ ተሞክሮ ይሆናል፡፡
ዜጎች የሌሎችን መብት አክብረው ሀሳባቸውን በነጻነት ሲገልጹ እና ሲያዳምጡ የግጭት እድሎች እየቀነሱ የመግባባት ባሕል ይጎለብታል። ይህ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ልምምድን የበለጠ የሚያሳድግ አካሄድ ነው፡፡
ዜጎች በውይይትና በምክክር ዘላቂ ሰላምን ሲገነቡ፣ ግጭትና ልዩነቶች እንዳይፈጠሩ በሮችን ሲዘጉ፣ ጊዜና ጉልበታቸውን ወደ ልማት እንዲያዞሩ ዕድል ይፈጥራል፡፡
ሰላም ካለ ሁሉም ዜጋ ፊቱን ወደ ልማት የሚያዞርበት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል፤ ልማት ሲኖር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከፍሬው የመቋደስ ዕድል ይኖረዋል፡፡
ስለሆነም ሀገራዊ ምክክሩ የሀገርን ሰላም በማፅናት ለዘላቂ ልማታ ፅኑ መሰረት የሚጥል ታሪካዊ አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡ ለስኬታማነቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የድርሻውን መወጣት ይጠበቅበታል፡፡
በቴዎድሮስ ሳህለ
Exit mobile version