አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአራቱም ማዕዘን ዛፍ እየተከለች፣ እየተንከባከበች እና ለፍሬ እያበቃች ትገኛለች።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ በተጠናከረ ዘመቻና ንቅናቄ እየተተገበረ የሚገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከ48 ቢሊየን በላይ የዛፍ ችግኞች እንዲተከሉ አስችሏል።
በዚህም የደን ሀብትን የሚያሳድጉ ዛፎች፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የፍራፍሬ ዛፎች፣ ለእንስሳት መኖነት የሚውሉ ዛፎች፣ የአፈር መከላትና መሸርሸርን የሚከላከሉ ዛፎች እንዲሁም የንብ ማነብ ስራን የሚያሳልጡ እጽዋቶች እንዲተከሉ ዕድል ፈጥረዋል።
እጅግ ተመናምኖ የነበረው የኢትዮጵያ የደን ሀብት አሁን ላይ ከመጥፋት ስጋት ተላቅቆ ሽፋኑ እያደገ መጥቷል። በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እውን መሆን የሀገሪቱ የደን ሽፋን 23 ነጥብ 6 በመቶ ደርሷል።
በፍራፍሬ ምርታማነትም እንዲሁ የሚጨበጥ ውጤት የተመዘገበ ሲሆን የፍራፍሬ ምርት ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ወደ ለውጭ ገበያ በስፋት ማቅረብ ተጀምሯል።
በእንስሳት መኖ አቅርቦትም የተገኘው ውጤት የእንስሳት ሀብት ልማትን በስኬት ለመምራት እያስቻለ ሲሆን፤ በንብ ማነብ ረገድ የማር ምርታማነትን ለመጨመር መርሐ ግብሩ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የዛሬን ብቻ ሳይሆን የነገውን ትውልድ ታሳቢ አድርጓል። መርሐ ግብሩ የደን ሽፋንን ከማሻሻል ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ያረጋገጡ ውጤቶች አስገኝቷል፡፡
አረንጓዴ ዐሻራ የመደመር መንግሥት የተሻለች ሀገር ለትውልዱ የማስረከብ ቁርጠኝነት ማሣያ ሲሆን፤ ዛሬን ብቻ ሳይሆን የነገውን ትውልድ ታሳቢ አድርጎ እየተተገበረ ይገኛል።
አረንጓዴ ዐሻራ እንደሀገር የውበት ምንጭ፣ የኢኮኖሚ ተደማሪ አቅም ነው። በዚሁ መሰረት እየተሰራ ባለው የታቀደ ስራ ውጤቱ በተግባር እየተገለጠ መጥቷል።
ይህ በተግባር የተደገፈ ግዙፍ የአረንጓዴ ልማት ጉዞ፣ ከኢኮኖሚያዊና የአካባቢ ጥበቃ ፋይዳው አልፎ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ኢትዮጵያን ትልቅ ክብር እና ተሰሚነት አጎናጽፏታል።
ኢትዮጵያ በመርሐ ግብሩ ያገኘችው ውጤት አሁን ላይ ዓለምን እየገጠመ ካለው የአየር ንብረት ለውጥ ፈተና አንጻር ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው። ኢትዮጵያውያን የዛፍ መትከልን ፋይዳ በውል በመገንዘባቸው ለመርሐ ግብሩ ስኬት በየዓመቱ በአስደናቂ ትብብር ዐሻራቸውን እያኖሩ ነው።
ዘንድሮም ከ8 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ችግኝ ለመትከል የተግባር እንቅስቃሴ ውስጥ የገቡ ሲሆን፤ በነገው ዕለት ብቻ ከ800 ሚሊየን በላይ ችግኝ በመትከል ዓለምን ለማስደመም ዝግጁ ሆነዋል።

