Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአቡ ዳቢ የ10 ሚሊየን ችግኝ እቅድ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዋና ከተማ የሆነችው አቡ ዳቢ በበረሃማ አካባቢዎቿ 10 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ማቀዷን አስታወቀች፡፡

በሰው ሰራሽ አስተውሎት በመታገዝ ይከናወናል የተባለው የአቡ ዳቢ የችግኝ ተከላ ፕሮጀክት በረሃማ ስፍራዎችን ወደ አረንጓዴነት ለመቀየር ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የሀገሪቱ የአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ እንዳስታወቀው÷ ለችግኝ ተከላ ተስማሚ የሆኑ ቦታዎችን ለመለየት የሚያገለግሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እንዲሁም የችግኝ እድገቱን ለመገምገም የሚያግዙ የክትትል ስርዓቶች ተዘጋጀተዋል፡፡

የ10 ሚሊየን ችግኝ ዕቅዱ አቡ ዳቢ ያሏትን ሀገር በቀል የዕፅዋት ዝርያዎችን ከጥፋት ለመታደግ፣ ብዝሃ-ህይወትን ለማጎልበት እና በሀገሪቱ እየተከሰተ ላለው የበረሀማነት መስፋፋት አዎንታዊ መልስ ለመስጠት ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡

እስካሁንም ጋፍ፣ ሳማር፣ አርታ፣ ሾአ፣ ራጋል እና ታማም የተባሉ አካባቢዎች የአፈር አይነት እና የጨዋማነት መጠናቸው ተለይቶ ለችግኝ ተከላው ዝግጁ ተደርገዋል ተብሏል፡፡

እንደ ዓለም አቀፉ የአካባቢ ጥበቃ መረጃ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የዝናብ እጥረት፣ ከፍተኛ ሙቀት፣ የበረሃማነት መስፋፋት፣ የግጦሽ መሬት እና የሀገር በቀል እፅዋቶች መመናመን ችግር የሚያጋጥማት ሀገር ናት፡፡

ችግሩን ለመከላከል ቀደም ሲል ሀገሪቱ በሰው ሀይል ብቻ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ስታደርግ የቆየች ሲሆን አሁን ላይ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ጨምሮ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የምታደርገው የችግኝ ተከላ ውጤት ሊያመጣላት ይችላል መባሉን ገልፍ ኒውስ ዘግቧል፡፡

በሚኪያስ አየለ

Exit mobile version