Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አረንጓዴ አሻራ የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ውጤታማ መሣሪያ ሆኗል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አረንጓዴ አሻራ የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ውጤታማ መሣሪያ ሆኗል አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
ከንቲባዋ የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ በመርሐ ግብሩ ባለፉት 7 ዓመታት ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸው በመደመር መንግሥትና በሕብረተሰቡ መካከል የተጠናከረ ትብብር የተመዘገበት ታሪካዊ ስኬት ነው ብለዋል።
ህም የዘመኑ ትልቅ ሀገራዊ ትሩፋት መሆኑን ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ከመርሐ ግብሩ ጅማሬ አንስቶ ከ90 ሚሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል ከፍተኛ ድርሻ ማበርከቷን ጠቅሰው፤ በ2018 ዓ.ም 6 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል እቅድ ተይዞ እስካሁን 5 ነጥብ 2 ሚሊየን ችግኞች መተከላቸውን ጠቁመዋል።
በዛሬው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ብቻ አንድ ሚሊየን ችግኞች እንደሚተከሉ ገልጸው÷ በሁሉም ክፍለ ከተሞች፣ ወረዳዎች፣ ብሎኮች፣ መንግሥታዊና የግል ተቋማት፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት እና የግል ኩባንያዎች በስፋት በመሳተፍ የተከላ ሥራውን እያከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።
በሕብረተሰቡ ሰፊ ተሳትፎ የተያዘው ዕቅድ ከታቀደው በላይ እንደሚሳካ ያላቸውን እምነት ገልጸው፤ የተከላ መርሐ ግብሩ የኢትዮጵያን የወደፊት ተስፋ በመገንባት ለምለሚቷን ኢትዮጵያ ለማረጋገጥ የሚያገለግል ሀገራዊ እንቅስቃሴ ነው ብለዋል።
ችግኝ መትከል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የአካባቢ ውበትን ለማሳደግ እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
በተለይም በአዲስ አበባ እየጨመረ የመጣውን የጎርፍ ተጋላጭነት ለመቀነስ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ውጤታማ መሣሪያ መሆኑን አመልክተዋል።
ችግኝ ከመትከል ባለፈ የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብና የመጠበቅ ኃላፊነት የሁሉም ዜጎች የጋራ አደራ መሆኑን በማስገንዘብ፣ የተፈጠረውን አረንጓዴ ሀብት በጋራ በመጠበቅ የመርሐ ግብሩን ዘላቂ ውጤት እንዲረጋገጥ ለሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ጥሪ አቅርበዋል።
በዮናስ ጌትነት
Exit mobile version