በ21ኛው ክፍለ ዘመን የአየር ንብረት ለውጥ፣ የደን መጨፍጨፍ፣ የውሃ እጥረትና የአፈር መራቆት የሰው ልጅ ዐቢይ ፈተናዎች በሆኑበት በዚህ ዘመን፣ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብራችን እነዚህን በምግብ ዋስትናና በኢኮኖሚ ላይ ያረፉ ጫናዎችን ለመቀልበስ ትልቅ አቅም ሆኖናል።
የነገን ትውልድ ለመታደግ በጀመርነው በዚህ ወሳኝ ሀገራዊ ተግባር ባገኘነው ውጤት፣ ቀድሞ ወደ 3 በመቶ ዝቅ ብሎ የነበረው የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በአረንጓዴ ዐሻራችን አማካኝነት አሁን ላይ 23 ነጥብ 6 በመቶ ላይ ደርሷል።
መርሐ ግብሩ የተመናመኑ ደኖቻችንን መልሶ በመተካት የተፈጥሮን ሚዛን እንድንጠብቅ አስችሎናል። በተከልናቸው ዛፎች አማካኝነት የምድራችንን ሙቀት በመቀነሱ ረገድ የጎላ ድርሻ እያበረከትን እንገኛለን።
የተከልናቸው ችግኞች በየዓመቱ ይባክን የነበረውን በሚሊዮን ቶን የሚቆጠር ለም አፈር ከመሸርሸር ታድገውልናል።
የዝናብ ውሃ ወደ መሬት ዘልቆ እንዲገባ በማድረግም የከርሰ ምድር ውሃችንን መጠን ማሳደግና የብዝሃ ህይወትን ደህንነት ማረጋገጥ ችለናል።
የአረንጓዴ ዐሻራ ጥረታችን ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ ትልቅ የኢኮኖሚ ፋይዳንም አስገኝቶልናል። በተለይም መርሃ ግብሩን ተከትሎ የተተከሉ የፍራፍሬ ዛፎችና የተለያዩ የደን ውጤቶች ለገበሬውም ሆነ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።
ሀገራችን ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ባደረገችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል አስደናቂ ውጤት አስመዝግባለች።
በአጠቃላይ በዚህ ስኬት የተፈጥሮ ሃብታችንንና ኢኮኖሚያችንን በማሳደግ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገርን የማስረከብ የዜግነት ግዴታችንን በተግባር እየተወጣን እንገኛለን።

