አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን ዳሞት ጋሌ ወረዳ ነዋሪዎች የተከልናቸው ችግኞች ጸድቀው ለፍሬ እስኪበቁ ድረስ ተገቢውን እንክብካቤ እናደርጋለን አሉ።
ነዋሪዎቹ “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል በአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኝ የመትከል መርሐ ግብር ዐሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡
በችግኝ ተከላው ላይ ተሳትፎ ያደረጉ ነዋሪዎች ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደገለጹት፤ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በንቃት እየተሳተፉ ነው።
ባለፉት ዓመታት በተካሄዱ የችግኝ ተከላ እንቅስቃሴ በንቃት በመሳተፍ ዐሻራቸውን ማኖራቸውን አስታውሰው፤ በመርሐ ግብሩ በተሰራው ስራ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤቶችን መመልከታቸውን ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ የዛፍ መትከልን ጥቅም በአግባቡ መገንዘብ መቻሉን ገልጸው፤ የዛፍ መትከልና መንከባከብ ባህል እያደገ መጥቷል ብለዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን መጨመሩን ጠቅሰው፤ በንብ ማነብና በእንስሳት ሀብት ልማት ሰፊ የስራ ዕድል እየተፈጠረ እንደሆነ ጠቁመዋል።

