አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የደሴ ከተማ ነዋሪዎች አረንጓዴ ዐሻራ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው አሉ
ነዋሪዎቹ “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል በአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኝ የመትከል መርሐ ግብር ዐሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡
ከችግኝ ተከላው በኋላ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በሰጡት አስተያየት፤ የደሴ ከተማ የመሬት መንሸራተት አደጋ ስጋት እንዳለበት አንስተዋል።
ይህንን ስጋት ለመቀነስ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኘው አረንጓዴ ዐሻራ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ወጣት ህሊና ፍቅሬ፤ የምትኖርበት አካባቢ በተፈጥሮው የመሬት አቀማመጡ የማይመች እንዲሁም የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋዎች የሚከሰቱበት በመሆኑ ችግኝ መተከሉ አደጋዎችን ለመቀነስ ያግዛል ብላለች፡፡
ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አብዱ ይማም በበኩሉ ችግኝ ባለመተከሉ የመሬት መንሸራተት ተጋላጭነት ሲያጋጥም ቆይቷል ብሏል።
በክረምት ወቅት አውራ ጎዳናዎችን ጨምሮ በመሬት መንሸራተት የተነሳ ችግር ሲያጋጥማቸው እንደነበረ አስታውሷል።
ችግሩ ለማስቀረት መሬቱን በጋቢዎን የማሰር ስራ መሰራቱንና አሁን ደግሞ ችግኝ በመትከል ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አስገንዝቧል።
የተከልኳቸውን እጽዋቶች ለመንከባከብ ዝግጁ ነኝ የምትለው ሰሚራ እሸቱ በበኩሏ፤ የምኖርበት አካባቢ የመሬት መንሸራተት የሚያጠቃው በመሆኑ እሱን ለማስቀረት አረንጓዴ ዐሻራ ወሳኝ ነው ብላለች።
አዛውንቷ ዘሀራ ገብረጻድቅ ደግሞ፤ ለትውልድ የሚተላለፍ ዐሻራቸውን ማስቀመጣቸውን ገልጸው፤ የሚተከለው ዛፍ የተፈጥሮ አደጋን የሚያስቀር መሆኑን ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ፣ ችግኝ መትከል ብቻ በቂ ባለመሆኑ በቀጣይ የመንከባከብ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
በእመቤት ሲሳይ

