አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብርና ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋ በ2018 ዓ.ም በኩታገጠም የለማ ማሳ 13 ሚሊየን ሄክታር ደርሷል አሉ።
የግብርና ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኩታገጠም እርሻ በመደመር ዕሳቤ ባለ አነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮችን አንድ ላይ በማደራጀት ይዞታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የእርሻ ስራቸውን በጋራ አቀናጅተው የሚያለሙበት አሰራር ነው ብለዋል።
ይህ አሰራር አርሶ አደሮች ተደራጅተው ሜካናይዜሽን፣ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ እና አግሮ ኬሚካሎችን ተጠቅመው ምርታማነትን በማሳደግ ትልቅ ውጤት በማስመዝገብ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በ2011 ዓ.ም የኩታገጠም እርሻ ሲጀመር 600 ሺህ ሄክታር በማልማት የተጀመረ ሲሆን በ2018 ዓ.ም በኩታገጠም የለማ ማሳ 13 ሚሊየን ሄክታር ደርሷል ብለዋል።
9 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚሆኑ አርሶ አደሮቻችንም በኩታገጠም እርሻ ተደራጅተው ማሳቸውን እያለሙ ሲሆን፤ በዚህም 29 በመቶ የምርታማነት ዕድገት ማስመዘገብ ችለዋል ሲሉ ገልጸዋል።
እነዚንህ የኩታገጠም እርሻዎች አዲስ በወጣው የግብርና ቢዝነስ ኩባንያዎች አዋጅ መሰረት በሕግ የተመዘገቡ፣ በሙያ የሚተዳደሩ የአርሶ አደሮች አግሪቢዝነስ ኩባንያዎች በመሸጋገር የአርሶ አደሮቻችንን ህይወት ለመቀየር፣ የግብርናውን ዘርፍ ወደ ከፍተኛ ተወዳዳሪነት ለማሸጋገር ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል።
አዲስ የሚቋቋሙት የአርሶ አደሮች የቢዝነስ ኩባንያዎች ባለ አነስተኛ ይዞታ አምራቾችን የቢዝነስ እሳቤ በማስፋት፤ ምርት የማሰባሰብ፣ እሴት የመጨመር እና በገበያ የመደራደር አቅማቸውን በማሳደግ የላባቸውን ዋጋ እንዲያገኙ ያደርጋል።
በተጨማሪም አነስተኛ አርሶ አደሮች ተደራጅተው ወደ መካከለኛ አልሚነት እና የአግሮ ፕሮሰሲንግ ስራዎች ለማሸጋገር የሚያስችል አማራጭ ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠር ያስችላል።

