Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የባሕር በር ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማት

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የባሕር በር ለማንኛውም ሀገር ከኢኮኖሚ፣ ከንግድ፣ ከደህንነት እና ከዓለም አቀፍ ግንኙነት አንፃር እጅግ ወሳኝ ሀብት ነው።
በዓለም ላይ አብዛኛው የዓለም ንግድ በባሕር መጓጓዣ ስለሚከናወን፣ የባሕር በር ያላቸው ሀገራት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት እንዲኖራቸው ያስችላል።
በተቃራኒው የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ከንግድ፣ ሎጂስቲክስ፣ ብሔራዊ ጸጥታ እና ከመሳሰሉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ተግዳሮቶችን ለመጋፈጥ ይገደዳሉ።
ኢትዮጵያ በታሪካዊ ጠላቶችና በውስጥ ባንዳዎች የተቀነባበረ ሴራ የባሕር በሯን እንድታጣ ከተደረገ በኋላ በብዙ ዘርፎች ፈተናዎችን እየተጋፈጠች ትገኛለች።
የባሕር በር ያላቸው ሀገራት ምርቶችን በቀላሉ ወደ ውጭ ለመላክ እና ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ይችላሉ፤ በዓለም ንግድ ተወዳዳሪ እንዲሆኑም ያስችላቸዋል፡፡
ይህ የንግድ መጠንን በማሳደግ የውጭ ምንዛሪ ገቢን እንዲጨምር ያግዛል።
በወደቦች አቅራቢያ የሚገኙ ፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃን በቀላሉ ማስገባት ይችላሉ፣ የተመረቱ ምርቶችንም በፍጥነት ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። ይህ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለኢኮኖሚ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
የባሕር በር በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ወጪ ቅነሳ ረገድ ከፍተኛ ሚናን ይጫታል፡፡
የባሕር መጓጓዣ ከአየር እና ከመንገድ መጓጓዣ ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ወጪ አለው። ስለዚህም ሸቀጦች በብዛትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቾች ለማድረስ ያስችላል።
የባሕር በር ያላቸው ሀገራት በሎጂስቲክስ ምቹ በመሆናቸው የውጭ ባለሀብቶችን በቀላሉ ይስባሉ። ይህም አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን፣ የሥራ እድሎችን እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ያበረታታል።
የባሕር በር የጂኦፖለቲካ ጠቀሜታው ከፍተኛ ሲሆን ወደብ ያላቸው ሀገራት በክልላዊና በዓለም አቀፍ ንግድ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። ይህም የዲፕሎማሲ አቅማቸውን እና የኢኮኖሚ ተፅዕኖአቸውን ያጠናክራል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር በማጣቷ የተጋፈጠችው ጉዳት ዘርፈ ብዙ ሲሆን ከዚህም መካከል ከፍተኛ የማጓጓዣ፣ የወደብ ኪራይ እና ተያያዥ ወጪዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባቸውንና ወደ ውጭ የምትልካቸውን ምርቶች በጎረቤት ሀገራት ወደቦች በመጠቀም ታጓጉዛለች። ይህ ተጨማሪ የትራንስፖርት እና የወደብ ክፍያዎችን ያስከትላል።
የማጓጓዣ ወጪ ሲጨምር የሚገቡ ሸቀጦች ዋጋ ይጨምራል። ይህ በተለይ ነዳጅ፣ ማሽነሪዎች፣ መድሃኒቶችና ሌሎች መሠረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት እና ዋጋ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባነቷ፣ በጎረቤት ሀገራት ወደቦችና ትራንስፖርት አገልግሎቶች ላይ እንድትመረኮዝ አድርጓታል።
ወደብ አልባነት የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነት መቀነስ የሚያስከትል ሲሆን የማምረቻ ወጪ ሲጨምር የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪነታቸው ይቀንሳል።
ኢንቨስተሮችና በንግድ የተሰማሩ ድርጅቶች የማጓጓዣ ወጪ ዝቅተኛ የሆነባቸውን ሀገራት ይመርጣሉ። ስለዚህ የባህር በር አለመኖር አንዳንድ ኢንቨስትመንቶችን ሊያዘገይ ወይም ወደ ሌሎች ሀገራት እንዲዞሩ ያደርጋል።
የባሕር በር ለሀገራት የኢኮኖሚ እድገት፣ የንግድ መስፋፋት፣ የኢንዱስትሪ ልማት፣ የውጭ ኢንቨስትመንት በመሳብ እና የክልላዊ ትስስርን በማጠናከር ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ አለው።
ኢትዮጵያ የባሕር በር በማጣቷ ከፍተኛ የማጓጓዣ ወጪ፣ የውጭ ጥገኝነት፣ የምርት ዋጋ መጨመር፣ የብሔራዊ ደህንነት እና የኢንቨስትመንት ተግዳሮቶችን ተጋፍጣለች።
የመደመር መንግሥት ይህ ከባድ ፈተና ማብቃት አለበት በሚል እሳቤ የባሕር በር ጥያቄ አንስቶ ምላሽ ለማግኘት በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
በዚህም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰላማዊ ውይይት፣ በኢኮኖሚያዊ ትብብር እና በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ተጠቃሚ ለመሆን ጥረቱ ቀጥሏል።
ኢትዮጵያ በዘላቂነት የባሕር በር ተዘግቶባት መቀጠል እንደማትችል በመገንዘብ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሀገሪቱን ፍትሃዊ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ መስራት ይገባቸዋል፡፡ መላው ኢትዮጵያውያንም ይህ ቁልፍ ብሔራዊ ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ በአንድነት መቆም አለባቸው፡፡
በአቤል ነዋይ
Exit mobile version