አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ሲኤንኤን የቴሌቪዥን ጣቢያ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚሊየኖችን ቤት ወደ ብርሃን የቀየረ ግድብ ነው ሲል ገልፆታል፡፡
በሲኤንኤን የኬንያ ተወካይ ዘጋቢ የሆነችው ቪክቶሪያ ሩባደሪ ባሰናዳችው ዘገባ÷ በአፍሪካ ቀዳሚው የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ ወደሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አቅንታ የተመለከተችውን የግድቡን እውነት አጋርታለች፡፡
ጋዜጠኛ ቪክቶሪያ በዘገባዋ÷ ግድቡን ኢትዮጵያውያን ያለማንም ድጋፍ በራሳቸው አቅም ገንብተው ለውጤት ማብቃታቸውን ገልፃለች፡፡
145 ሜትር ከፍታ እና 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ ለቀጣናው የሀይል አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ተንትናለች፡፡
ግድቡ ከራስ ፍጆታ እስከ ቀጣናዊ የሀይል ትስስር እንዲሁም እስከ ቱሪስት መዳረሻነት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በማሳደግ ረገድ ዘርፈ ብዙ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ገልፃለች፡፡
በሲኤንኤን የሕዳሴ ግድብ ዘገባ ላይ በማጣቃሻነት የተጋበዙት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ÷ ግድቡ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ሀይል የማመንጨት አቅም እንዳለው አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ግድቡን የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት በማይጎዳ መልኩ እየተጠቀመች ነው በማለት ገልጸው÷ ግብፅ በግድቡ ምክንያት የሚደርሳት ውሃ ቀንሷል በሚል የምታቀርበው ክስ መሰረተ ቢስ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የአንደኛው ጥሩ ነገር ለሌላው መጥፎ ሊሆን እንደማይችል በመግለፅ፣ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም መብት እንዳላት፣ ሌሎች ሀገራትን ግን ተፅዕኖ እንዲደርስባቸው የማድረግ ፍላጎት እንደሌላት አብራርተዋል፡፡
አሁን ላይ በሕዳሴ ግድቡ የሚገኙ 13 ተርባይኖች በሚያመነጩት ሀይል 6 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ ጎረቤት ሀገራትን የኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን በመጠቅሰ ሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ እና ታንዛኒያ ሀይል ተደራሽ ማድረግ መቻሉን፣ በቀጣይ ደግሞ ለሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ሀይል ለመሸጥ ዝግጅት መደረጉን አመላክተዋል፡፡
በተጨማሪም በሕዳሴ ግድቡ ወደ 72 ሚደርሱ ደሴቶች እና ሀይቆች መፈጠራቸውን ጠቁመው፤ እነዚህ ስፍራዎች ለቱሪስት መስህብነት የሚውሉ መሆናቸውን ነው ያስገዘነቡት፡፡
በቀጣይም ለቱሪስት መዳረሻነት የሚያገለግሉ መሰረተ ልማቶች እንደሚገነቡ በመግለፅ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከኤሌክትሪክ ሀይል በተጨማሪ የቱሪስቶች መዳረሻ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ

