Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አረንጓዴ ዐሻራ – ለትውልድ የሚሸጋገር ትልቅ ሀብት

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገር የመሬት ገጽ፤ የተፈጥሮ ጸጋዎች ወይም የድንበር መስመር ብቻ ሳትሆን፣ የሕዝቧ የጋራ ሕልምና የአንድነት ውጤት ናት።
አንድ ሕዝብ ለአንድ በጎ ዓላማ በጋራ ሲቆም ተራራዎችን ንዶ ለጥ ያለ ሜዳ ማድረግ፤ ከጠብታ ውሀ እልፍ ምድርን ማልማት በአጠቃላይ የማይቻሉ የሚመስሉ ነገሮችን እውን ማድረግ እንደሚችል ታሪክ ደጋግሞ አሳይቷል።
ለዚህም ትልቁና ቅርቡ ማረጋገጫችን ትላንትና የኢትዮጵያ ህዝብ ህጻን አዋቂ፤ ሴት ወንድ ሳይል የከወነው፤ በዓይናችን ያየነው፣ ለመላው ዓለምም ትልቅ ተምሳሌት የሆነው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ ታሪካዊ ቀጠሮ ነው።
በትናንትናው ዕለት ኢትዮጵያ ያካሄደችው የአንድ ጀምበር ችግኞችን የመትከል ተግባር ተራ የዛፍ ተከላ መሰናዶ ብቻ አልነበረም።
ይልቁንም ኢትዮጵያውያን በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በዕድሜና በጾታ ሳይለያዩ በአንድ ዓላማ ስር የተሰለፉበት፤ የጋራ ቤታቸውን አረንጓዴ ሸማን ለማልበስ በወንድማማችነትና በእህትማማችነት ስሜት ከጫፍ ጫፍ የዘመቱበት ታሪካዊ ዕለት ነበር።
ሕዝብ በአንድ በጎ ዓላማ ዙሪያ ሲሰባሰብ ምን ያህል ፈጣንና ውጤታማ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል የአረንጓዴ ዐሻራ ጅማሮውን ካደረገበት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በተሰሩ ስራዎች በተግባር ታይቷል።
ይህ የህዝብ ህብረትና ለአንድ ዓላማ በአንድነት መቆም ለኢትዮጵያውያን አዲስ አይደለም፡፡
ለዚህ ማሳያ የዓድዋ ድልን ማንሳት ይቻላል፤ ወራሪ ጠላትን ኢትዮጵያውያን ከጫፍ ጫፍ በመሰባሰብ ድል እንደነሱት ሁሉ፤ የአረንጓዴ ዐሻራም “ብዙ ሆነው ሲገፉት ተራራም ይንቀሳቀሳል” የሚለውን ሀገራዊ ብሂል በገሀድ ለዓለም ያሳዩበት ነው፡፡
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከዚህ ዘመን አልፎ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር የአረንጓዴ ሀብት ተስፋ ለነገይቷ ሀገር ጠንካራ መሠረት ጥሏል።
የአረንጓዴ ዐሻራ ዘመቻ የሚያስተላልፈው ትልቁ መልዕክት ከተባበርን የማይቻል የለም የሚለውን እውነት ነው።
በአንድ ጀምበር ሚሊየኖችን አሰልፎ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን መሬት ማልበስ ከተቻለ፣ ያንኑ የአንድነትና የትብብር መንፈስ በሌሎች የሀገራችን ዘርፎች ላይ በመጠቀም ምን ያህል ትልቅ ታሪክ መስራት እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ ሁነት ነው፡፡
የአረንጓዴ ዐሻራ ዘመቻ ኢትዮጵያውያን ከተባበሩ የማያሸንፉት ፈተና፣ የማይሻገሩት ድንበርና የማይጽፉት ታሪክ እንደሌለ ያሳየ ታላቅ ምስክር ነው።
በመልካም ፈቃዱ
Exit mobile version