አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ሲኤንኤን የቴሌቪዥን ጣቢያ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት በአፍሪካ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ግዙፍ ፕሮጀከት ነው አለ፡፡
በሲኤንኤን የኬንያ ተወካይ ዘጋቢ የሆነችው ቪክቶሪያ ሩባደሪ ባሰናዳችው ዘገባ÷ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካውያንን ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በማገናኘት እጅግ ስኬታማው አየር መንገድ መሆኑን ገልጻለች፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ራሱን ይበልጥ ለማሳደግና ተደራሽነቱን ለማስፋት የቢሾፍቱ አየር መንገድ ግንባታ ፕሮጀክትን ይፋ ማድረጉን በማንሳት፤ የአየር መንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ በአፍሪካ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን አብራርታለች፡፡
ነገሮች በታቀዱት መንገድ የሚሄዱ ከሆነ በ2030 የአየር መንገዱ ግንባታ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም ጠቅሳለች፡፡
የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ከ12 ቢሊየን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነባ ሲሆን የኢትዮጵያን አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን የሚደግፍ መሆኑንም በዘገባዋ አመልክታለች፡፡
አየር መንገዱ የማክሮ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በመሆን ማገልገል የሚችል ሲሆን፤ በተለይም ንግድ እና ቱሪዝምን በማሳለጥ ረገድ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁማለች፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ከጋዜጠኛዋ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓመት 22 ሚሊየን ዓለም አቀፍ ደንበኞች በረራ ያደርጋሉ ብለዋል፡፡
የተጓዥ ደንበኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ መበራከት የአየር መንገዱን የማስተናገድ አቅም በመፈታተኑ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን ለማስጀመር መገዳዳቸውንም ጠቁመዋል፡፡
የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪውን በኢትዮጵያ ብሎም በአህጉሪቱ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድገው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቻይና እና የእሲያ መደራሻዎች ከሌሎች ዓለማት አንጻር በቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ ሆኖም የአየር መንገዱን ዓለም አቀፍ ተደራሽነት ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በቢሾፍቱ አቡሴራ የሚገነባው ግዙፉና ዘመናዊው አውሮፕላን ማረፊያ የካርጎ ተርሚናል የዓለም የንግድ ዕቃዎች እና የህክምና አቅርቦቶች ከአምራች ሀገራት ተነስተው ወደ ተጠቃሚዎች የሚሰራጩበት ዋነኛ የአየር ሎጂስቲክስ ማዕከል እንዲሆን ያደርገዋል።
እንደ አበባ፣ ፍራፍሬ እና ስጋ ያሉ የኢትዮጵያና የጎረቤት ሀገራት ምርቶች ሳይበላሹ በጥራትና በከፍተኛ ፍጥነት ወደ መላው ዓለም ገበያ እንዲደርሱ ያስችላል። ይህም ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የአየር ጭነት ማዕከልነቷን የሚያረጋግጥ ይሆናል፡፡
ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ኢንደስትሪ ውስጥ እንደ ዱባይ (DXB) እና ሲንጋፖር (Changi) ያሉ ታላላቅ የዓለም መገናኛ ማዕከላት ተርታ ያሰልፋታል።
ኢትዮጵያን የአፍሪካ ቁልፍ የአቪዬሽን መናኸሪያ በማድረግ ከአህጉራዊ የትራንዚት ማዕከልነት ወደ መላው ዓለም ስልታዊ መገናኛ ድልድይነት ያሸጋግራል፡፡
በአቤል ነዋይ

