አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበረሰብን ለማጠናከርና ሀገራዊ አንድነትን ለማጽናት ወሳኝ የሰብዓዊነት መገለጫ መንገድ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በክረምት ወቅት ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ በመሰማራት ማህበረሰባቸውን በማገልገል ለሀገራቸው ያላቸውን ቁርጠኝነት እያሳዩ ይገኛሉ፡፡
ይህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የትውልድን አስተሳሰብ በማጽናት የሀገርን የወደፊት መንገድ ለማቃናት ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ ወጣቶች በመማር ያገኙትን እውቀት የተግባር ልምምድ የሚያደርጉበት መድረክም ሆኗል፡፡
ወጣቶች እንዲህ ባሉ ተግባራት ላይ በሚሰማሩበት ወቅት በጋራ ተቻችሎ የመስራትን፤ ችግር የመፍታት ክህሎትን እንዲያዳብሩ ከማስቻል ባለፈ በራስ የመተማመን ስሜትንና ለሀገር የመቆም ወኔን እንዲያዳብሩ ያግዛል፡፡
የበጎ ፈቃድ ተግባር የባሕል፣ ሀይማኖትና የአመለካከት ልዩነትን ከግምት ባላስገባ መልኩ የሚካሄድ ከመሆኑ ባሻገር ወጣቶች ተንቀሳቅሰው ሌሎች ወገኖቻቸውን ሲያግዙ እርስ በእርስ የመረዳዳት እና የመከባበር ባህል ይጎለብታል።
ይህም ወንድማማችነትን በመፍጠር ለሀገራዊ አንድነት እና ሰላም መረጋገጥ ሰፊ አስተዋፅኦ አለው።
ወጣቶች በዚህ ወቅት አቅመ ደካሞችን የመደገፍ፣ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እና የደም ልገሳ ላይ የመሳተፍ እንዲሁም ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት የመስጠት ተግባራትን እያከናወኑ ነው፡፡
በጎ ፈቃደኝነት ወጣቶች በሀገራቸውና ማህበረሰባቸው ላይ ባለቤትነት እንዲሰማቸው ያግዛል። ችግሮችን ከመተቸት ይልቅ የችግሩ መፍትሔ አካል የመሆን አስተሳሰብን በመፍጠር ረገድ ሚናው ትልቅ እንደሆነም ይታመናል፡፡
የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድር ሲሆን፤ እንደ ሀገር ሊወጣ የሚችለውን ከፍተኛ ወጪ በመቆጠብ የበርካታ ዜጎችን ሕይወት በቀጥታ ለማሻሻል ይረዳል፡፡
በበጎ ፈቃድ የሚሳተፍ ትውልድ መፈጠሩ ነገ ሀገርን በቅንነት እና በታማኝነት የሚያገለግሉ መሪዎችንና ባለሙያዎችን ለማፍራት ትልቅ መሰረት ይጥላል።
በጎ ፈቃደኝነት የዛሬን በጎ ተግባር በመስራት የነገዋን የተሻለች ኢትዮጵያ የመገንቢያ ወሳኝ መንገድ በመሆኑ፤ የኢትዮጵያ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚያሳዩት ተሳትፎ የኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።
በቤተልሔም ግርማ

