አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሥነ-ልክ ቀጣዩን የአፍሪካ ልማት በጥራት ላይ የተመሰረተ ለማድረግ ወሳኝ ነው አሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)።
19ኛውን የአፍሪካ ሥነ-ልክ ድርጅት (AFRIMETS) ጠቅላላ ጉባኤ “ሥነ-ልክ ለዲጂታል ሽግግር፡ ተዓማኒ ልኬቶች ለአፍሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታ” የሚል መሪ ሐሳብ የተለያዩ ሀገራት እና ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት በኢትዮጵያ የጥራት መንደር ውስጥ እየተካሄደ ነው።
ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በጉባኤው እንዳነሱት፤ ሥነ-ልክ ቀጣዩን የአፍሪካ ልማት በጥራት ላይ የተመሰረተ ለማድረግ ወሳኝ ነው።
አፍሪካ በዓለም አቀፍ ገበያ ስኬታማ ውድድር ማድረግ እንድትችል በጋራ ልማት እና ጥራት ላይ የተመሰረተ ትስስር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
የሀገራትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጠንካራ ተቋማትና ብቁ ባለሙያዎችን ማፍራት እንደሚገባም ጠቅሰዋል።
የአፍሪካ ሥነ ልክ ድርጅት ሊቀመንበር ሄንሪ ሮቲች (ዶ/ር) አገልግሎቶች ሁሉ ወደ ዲጂታል ስርዓት ባመሩበት በዚህ ወቅት ሥነ-ልክ ወሳኙ የትኩረት ማዕከል መሆን እንዳለበት አንስተዋል።
ምድረ ቀደምት የሆነችው ኢትዮጵያ በተለያዩ ማዕቀፎችም አሰባሳቢነቷ ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ የጥራት መንደር መሰረተ ልማት ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን ቀጣይ የልማት መዳረሻ የሚያመላክት መሆኑን ገልጸዋል።
መሰረተ ልማቱ ለአፍሪካዊያን ፈር ቀዳጅ የተሞክሮ ስፍራ እንደሚሆን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ሥነ ልክ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሙሉጌታ ደርበው (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የዘርፉን አገልግሎት ዘመኑን በሚመጥን አቅም መገንባት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ጉባኤው በአህጉሪቱ የጥራት መሰረተ ልማትን ውጤታማ በሆነ መልኩ እውን ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በአሸናፊ ሽብሩ

