ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አረንጓዴ አብዮትን እና የምግብ ሉዓላዊነትን እያረጋገጠች ነው።
ባለፉት ሰባት ዓመታት ብቻ በዘርፉ በተሰራው ሥራ የደን ሽፋንን ከ17 በመቶ ወደ 23.6 በመቶ ማሳደግ ተችሏል፡፡
እውነተኛ የሀገር ሉዓላዊነት የሚለካው በድንበር ብቻ ሳይሆን ሕዝብን በራስ አቅም በመመገብና የተፈጥሮ ሀብትን በዘላቂነት መጠበቅ ሲቻል ነው፡፡
በአረንጓዴ አሻራ ታዲያ በየዓመቱ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን በነቂስ በማስተባበር የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ነፃነት እና የነገ ተስፋ በጽኑ መሠረት ላይ ማቆም እየተቻለ ነው።
ኢትዮጵያውያን በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እያሳዩት ያለው አንድነት፣ ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ ሰፊ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አንደምታዎች አሉት፡፡
ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ብቻ በአንድ ጀምበር 805.3 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል ኢትዮጵያ ከአረንጓዴ አሻራ ወደ እውነተኛ አረንጓዴ አብዮትና ሉዓላዊነት ለመሸጋገር እያደረገች ያለችውን ጉዞ በአግባቡ ያሳየ ተግባር ሆኗል፡፡
በየአመቱ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች ከአንድ ዓላማ በስተጀርባ መሰለፍ መቻላቸው ህዝባዊ አንድነትንና አብሮነትን ያሳያል፡፡
በተለይም አዲሱ ትውልድ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ የመኖርና የመንከባከብ ባህል እንዲያዳብር ትልቅ ትምህርት ሆኗል።
ይህ ተግባር ኢትዮጵያ ለዓለም የአየር ንብረት መጠበቅ የምታበረክተውን ድርሻ ከፍ አድርጎታል። ዛፎቹ እያደጉ ሲሄዱ ደግሞ ሀገሪቱ ከዓለም አቀፍ የካርቦን ሽያጭ ሰፊ የፋይናንስ ተጠቃሚ እንድትሆን በር ይከፍታል።
በበጋ መስኖና በመስኖ ግድቦች የታገዘው ሀገራዊ የስንዴ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ጥረት የውጭ ጥገኝነትንና የስንዴ ተመጽዋችነትን በዘላቂነት እየፈታ እንዳለው ሁሉ፣ አረንጓዴ አሻራም ግቡ ከአካባቢ ጥበቃ በላይ እየሆነ ነው፡፡
የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ መጀመሪያ ላይ ተፈጥሮን ከመራቆት የመታደግ ሀገራዊና ቀጣናዊ ዘመቻ ነበር።
ዛሬ ግን ይህ ርብርብ ፊቱን ወደ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት አዙሯል፡፡ ህዝባዊ አንድነትንና ለሀገራዊ ሉዓላዊነት በጋራ መጽናትን አስተምሯል፡፡
እንደ ቡና፣ አቮካዶ፣ ማንጎ እና አፕል ያሉ ተክሎች ለምግብ ዋስትና እና ለውጭ ንግድ ገቢ እያገለገሉ ነው።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶችና ሴቶች በተሳተፉበት መልኩ አረንጓዴ የስራ እድሎች በሰፊው እየተፈጠሩ ነው፡፡
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ አረንጓዴ አብዮት የነገዋን የበለጸገችና ራሷን የቻለች ሀገር ለመገንባት የተጣለ ጽኑ መሠሰረት ነው።
ችግኞችን ከመትከል ባለፈ በተደራጀ መልኩ የመንከባከብና የመጠበቅ ባህል ማደጉ፣ ይህ ህዝባዊ ንቅናቄ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር ዘላቂ ድል መሆኑን ያረጋግጣል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት እያስመዘገበች ያለችው ስኬት በተግባር የተደገፈ እውነተኛ የሉዓላዊነት ማረጋገጫ ማሳያ ነው።

