Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከሀገራዊ ደህንነት እስከ ኢንዱስትሪ ልማት

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ21ኛው ክፍለ ዘመን የአንድ ሀገር የመከላከያ ጥንካሬ በሠራዊቱ ብዛት ወይም በሚገዛቸው መሳሪያዎች ብቻ አይለካም።
ኢትዮጵያ ከለውጡ በኋላ የመከላከያ ኢንዱስትሪዋን ለማጠናከር እና በመሳሪያ ራሷን ለመቻል የተለያዩ ዕቅዶችን እየተገበረች ትገኛለች።
ይህ ሂደት ከመከላከያ በተጨማሪ በኢንዱስትሪ፣ በቴክኖሎጂ፣ በሳይንስ እና በኢኮኖሚ ላይ ዘርፈ ብዙ ውጤት ለማምጣት ያግዛል፡፡
ኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ ጥገና እና የጥይት ምርት ላይ ለብዙ አስርት ዓመታት ስትሰራ ቆይታለች።
በተለይ የጦር መሳሪያ ጥገና፣ የታንክና የመኪና ጥገና፣ የአውሮፕላን ጥገና እና የጥይት ማምረት በሀገሪቱ የቆዩ ዘርፎች ናቸው።
በመደመር መንግሥት ደግሞ በራስ አቅም የማምረት እና የቴክኖሎጂ ልማት ላይ የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡
በተለይም የጥይት ምርት መጨመር፣ የጦር መሳሪያ ጥገናን በሀገር ውስጥ ማከናወን፣ የውጊያ ተሽከርካሪዎችን ማሻሻል፣ የድሮን ቴክኖሎጂ ላይ አቅም መገንባት እና የመከላከያ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ማስፋፋት የሚሉ ጉዳዮች ተጠቃሽ ናቸው።
አሁን ላይ ዘመናዊ ጦርነቶች በዋነኝነት በድሮኖች፣ በመረጃ ቴክኖሎጂ፣ በሳተላይት መረጃ እና በኤሌክትሮኒክ ሥርዓቶች ላይ እየተመሰረቱ ነው።
የመከላከያ ኢንዱስትሪ ማደግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን የውጭ ምንዛሬ ወጪ መቀነስ፣ የስራ እድል መፍጠር፣ የብረት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ኬሚካል እና ሶፍትዌር ኢንዱስትሪዎች ማደግ እና የዩኒቨርሲቲ ምርምር ከኢንዱስትሪ ጋር ማገናኘት የሚሉት በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የመከላከያ የመሳሪያ ማምረት አቅም መጨመር ለኢትዮጵያ የሀገራዊ ደህንነት ብቻ ሳይሆን ለኢንዱስትሪ እድገት፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ለሰው ኃይል ልማት እና ለኢኮኖሚ አቅም መጠናከር ወሳኝ ነው።
በተጨማሪም ሀገሪቱ በቀጣናዊ ወታደራዊ ሚዛን ውስጥ ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት የሚያጠናክርና ራስን በራስ የማስቻል ጉዞን ያፋጠነ ተግባራዊ ማሳያ ነው።
በአመለወርቅ ደምሰው
Exit mobile version