አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአንድ በኩል አፈርና ችግኝ የጨበጡ እጆች፤ በሌላ በኩል ደግሞ በምክክር አዳራሽ ውስጥ የነገዋን ሀገር ተስፋ የሚቅርጹ ድምፆች መሳ ለመሳ ሆነው የነገዋን ኢትዮጵያ ህያው ገጽታ እየገነቡ ነው።
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ አካባቢዋን ከመንከባከብና ከመጠገን ባሻገር፣ ለዘመናት የላላውን የማህበራዊ ግንኙነት ምሰሶ መልሶ ለመጠገን አዲስና የተቀናጀ የታሪክ መንገድ ላይ ትገኛለች።
በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ችግኞችን ከመትከል ጀምሮ የሀገራዊ የደን ሽፋንን በማሳደግ መላው ኢትዮጵያውያን በጋራ ታሪክ እየጻፉ ነው፡፡
በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የሀገራዊ ምክክር ሂደትና የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የነገዋን ኢትዮጵያ ህልም የሚገነቡ ሁለት ዋና ዋና መሰረቶች ሆነዋል፡፡
በመጀመሪያ እይታ ችግኝ መትከልና ለሀገራዊ ምክክር መቀመጥ የተያያዙ ባይመስሉም፣ በይዘታቸው ግን አንድ ዓይነት ጥልቅ እውነትን ይጋራሉ፤ ሁለቱም ትዕግስትን፣ አክብሮትን እና የወደፊት ተስፋን መዝራት ይጠይቃሉ።
ችግኝ ተክሎ ውሃ እንደማጠጣት ሁሉ፤ ሀገራዊ ምክክርም ፍሬ የሚያፈራው እርስ በእርስ በመደማመጥና በመከባበር ነው፡፡
በጠዋት በጋራ ችግኝ ተክሎ ከሰዓት በኋላ በሀገር ጉዳይ ላይ መምከር በዜጎችና መካከል ጠንካራ የመደጋገፍና የመተማመን ስሜት ፈጥሯል፡፡
በየአካባቢው በአፈር ላይ ያረፉት የዜጎች ዐሻራ ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ብቻ ሳይሆን፣ በጋራ መስራት እና በሰለጠነ መንገድ መነጋገር ይቻላል የሚል ትልቅ የስነ ልቦና ጥንካሬና ተስፋ ይሰጣል።
ይህ ተፈጥሮን የማለምለም እና የሰዎችን ልብ የመክፈት ጥበብ፣ ጎን ለጎን እየተሳለጠ የኢትዮጵያን የነገ ተስፋ በፅኑ መሰረት ላይ በጥበብ እየገነባ ይገኛል።
በአብረሃም አበራ

