አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ከምታከናውናቸው ሥራዎች ውስጥ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ቀዳሚው ነው፡፡
በተለይም በግብርና እና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያለውን ምርታማነት ይበልጥ ለማሳደግ የመደመር መንግሥት የተለያዩ ኢኒሼቲቮችን በመቅረጽ እየተገበረ ይገኛል፡፡
ከእነዚህ ንቅናቄዎች ውስጥም በምግብ ራስን ለመቻልና የሥርዓተ ምግብ ጥራትን ለማሻሻል የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊ የእንስሳት ሃብት ያላት ሀገር ብትሆንም ከዘርፉ የምታገኘው ጥቅም ግን ዝቅተኛ ነበር፡፡
ከአራት ዓመት በፊት የተጀመረው የሌማት ትሩፋትም በእንስሳት ሃብት ልማት ዘርፍ የወተት ምርታማነትን በከፍተኛ መጠን በማሳደግ የምርቱን ፍላጎት ለማሟላትና የውጭ ምንዛሪን ለማዳን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡
የሌማት ትሩፋት በዋናነት የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥና ክብርን ለማስጠበቅ ያለመ ሲሆን ÷ በተለይም ወተት፣ እንቁላል፣ ዓሳ፣ ማርና ስጋ ትርፍ ምርት ሆነው እንዲገኙ ማልማትና መጠቀምን መሰረት ያደረገ ነው።
በመርሐ ግብሩ የወተት ምርታማነትን ለማሳደግ ከተከናወኑ ሥራዎች ውስጥ የወተት ላም ዝርያን ማሻሻል ይጠቀሳል፡፡ ይህም የወተት ምርትን በብዛትና በጥራት በማሳደግ ረገድ ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡
የወተት ምርታማነትን በማሳደግ ከውጭ ይገባ የነበረን የወተት ምርት በሀገር ውስጥ በመተካት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማዳን ተችሏል፡፡ከዚህ ባለፈም በሀገር ውስጥ የወተት ምርት አቅርቦትን በከፍተኛ ሁኔታ በማጠናከር በርካታ የሥራ እድሎች ተፈጥረዋል፡፡
የሌማት ትሩፋት ሲጀመር በዓመት 7 ነጥብ 1 ቢሊየን ሊትር ወተት ብቻ ይመረት የነበረ ሲሆን÷ አሁን ላይ ግን በመርሐ ግብሩ በዓመት የሚመረተው ወተት ከእጥፍ በላይ በመጨመር ወደ 15 ነጥብ 7 ቢሊየን ሊትር ደርሷል፡፡
በ2018 በጀት ዓመት ብቻ የእንስሳት ዝርያን ለማሻሻል በተሰራ የማዳቀል ሥራ ከ4 ነጥብ 35 ሚሊየን በላይ ላሞችን ማዳቀል ተችሏል፤ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ጥጃዎችም ተወልደዋል፡፡
በዚህም ከ1 ነጥብ 57 ሚሊየን በላይ አርሶ እና አርብቶ አደሮች የተሻሻሉ የወተት ላሞችን በመጠቀም የወተት ምርታማነታቸውን አሳድገዋል፡፡
በሌላ በኩል በሌማት ትሩፋት የተመረተው ምርት በተገቢ ሁኔታ ለገበያ እንዲቀርብ የተከናወኑት ሥራዎች አበረታች ናቸው፡፡ አርሶ አደሮች የወተት ምርታቸውን ያለ ምንም እንግልት በተመጣጣኝ ዋጋ ለፋብሪካዎች እንዲያስረክቡ የገበያ ትስስር ተፈጥሯል፡፡
የገበያ ሰንሰለቱ የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ እንዲሆንም በተዋረድ አስፈላጊው ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል፡፡
የወተት ምርት ጤንነቱ ተጠብቆ ለገበያ እንዲቀርብ ማቀዝቀዣ የተገጠመላቸው ተሽከርካሪዎች ወተት በብዛት በሚመረትባቸው አካባቢዎች ላይ እንዲሰማሩ ተደርጓል፡፡
በምርቱ የገበያ ሰንሰለት ውስጥ ጣልቃ በመግባት አላስፈላጊ ተግዳሮት የሚፈጥሩ ሕገ ወጥ ደላላዎች ላይም አስፈላጊው ርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡
በተጨማሪም የወተት ምርታማነትን ለማሳደግ መሰረት የሆነውን የእንስሳት መኖ ጥራትና አቅርቦት ለማሻሻል የተከናወኑ ሥራዎች አመርቂ ውጤት አስገኝተዋል፡፡
በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር በወተት ምርት ላይ የተገኘው እመርታ በሀገር ውስጥ የወተት አቅርቦትን በመጨመር የተመጣጠነ ምግብን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡ በወተት ተዋጽኦ ምርቶች ማቀነባበርና ሌሎች ዘርፎች ያስገኘው የሥራ እድልም የሚደነቅ ነው፡፡
ስለሆነም በኢትዮጵያ ያለውን እምቅ የእንስሳት ሃብት ግምት ውስጥ በማስገባት ከዘርፉ የሚገኘውን ውጤት ይበልጥ ለማሳደግ በሌማት ትሩፋት የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል፡፡
በመላኩ ገድፍ

