Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በምክክር ውስጥ ሰጥቶ የመቀበል መርህ፡ የሀገር ህልውና እና የጋራ መግባባት መሠረት ነው

ማንኛውም ማህበረሰብም ሆነ ሀገር ዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋት እና እድገትን ማረጋገጥ የሚችለው ልዩነቶቹን በሰለጠነ መንገድ መፍታት ሲችል ብቻ ነው።
በፖለቲካውም ሆነ በማህበራዊ መስተጋብሮች ውስጥ የሚስተዋሉ አለመግባባቶችን ለማጥበብ ምክክር ዋነኛውና ተመራጭ መፍትሄ ነው።
ኢትዮጵያውያንም ይህንን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የዘመናት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እየመከሩ ነው፡፡
እየተካሄደ ባለው በዚሁ ሀገራዊ ምክክር ተሳታፊ የሆኑ አካላት በቅንነት፣ በግልጽነት እና በጋራ የመስራት መንፈስ ወደ ጠረጴዛ በመምጣት እየመከሩ ይገኛሉ፡፡
የዚህ አይነቱ ምክክር ዋነኛ ምሰሶ ደግሞ ሰጥቶ የመቀበል መርህ ነው።
ይህ ፅንሰ-ሀሳብ የራስን ፍላጎት ብቻ ከማስከበር ይልቅ ለሀገርና ለወገን ሲባል እውነትን ፍለጋ ወደ አማካይ ስፍራ የመምጣትን አስፈላጊነት ከግንዛቤ አስገብቷል፡፡
ኢትዮጵያውያን እያካሄዱት ያለው ሀገራዊ ምክክር በአንድ ወገን ፍላጎትና ግፊት ብቻ የሚወሰን ሂደት ባለመሆኑ፣ እኩል ተሳትፎና እውቅናን የሚጠይቅ ሰጥቶ የመቀበል መርህን ተግባር ላይ እያዋሉ ነው።
በምክክር የፖለቲካ ኃይሎችም ሆኑ የተለያዩ የማህበረሰብ ተወካዮች ወደ ውይይት ጠረጴዛ እየመጡ ያሉት የራሳቸውን ሀሳብ ብቻ በሌሎች ላይ ለመጫን ሳይሆን፣ የሌላውንም ወገን ስጋት፣ ፍላጎትና እይታ ለመስማት ዝግጁ በመሆን ነው።
ወደ ጠረጴዛ መቅረብ የራስን አቋም ብቻ ለማጽደቅ መሞገት ስላልሆነ፣ የሀገርን ህልውና እና ህዝባዊ ጥቅም ሊያድን ወደሚችል አማካይ ስፍራ እየተመጣ ነው፡፡
ይህ የተመካካሪዎች ሀገራዊ ስሜት፣ እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ የሚለውን አስተሳሰብ ሰብሯል።
በምክክር ሂደቱ፣ ሀሳቦች የሚሸነፉትም ሆነ የሚያሸንፉት በምክንያት እና በጋራ መግባባት መሆኑ ከግንዛቤ ገብቷል።
እያንዳንዱ ተመካካሪ የሚያቀርበው ሀሳብ በምክንያታዊነት እየተመዘነ፣ የትኛው ሀሳብ ለጋራ ሰላምና ለሀገር ደህንነት እንደሚጠቅም በግልጽ እየታየ የጋራ አቋም እየተያዘ ዛሬ ላይ ተደርሷል።
በዚህ ሂደት ውስጥ ማንም ሰው ወይም ቡድን 100 በመቶ ፍላጎቱን ብቻ ሊያሳካ አይችልም።
ተመካካሪው ፍፁም የሆነ የራስን ፍላጎት ብቻ የመጫን ዝንባሌ ዘላቂ ሰላም እንደማያመጣ ያውቃል፡፡
ለሀገር፣ ለወደፊት ትውልድ እና ለጋራ ህልውና ሲል አማካይ መገናኛ መስመር እየመረጠ ነው፡፡
ይህም ምክክሩ ፍሬያማ እና ዘላቂ መፍትሄ እንዲያመጣ ያደርገዋል፡፡
በአጠቃላይ ሀገራዊ ምክክሩ የሀገርን የፖለቲካ እና የማህበራዊ ቀውሶች ለመፍታት የሚያገለግለውን ሰጥቶ የመቀበል መርህ ተግባር ላይ እያዋለ ነው፡፡
ሀሳቦች በምክንያት ተሸንፈውና አሸንፈው የጋራ መግባባት ላይ ሲደረስ፣ ሀገራዊ መግባባት ይፈጠራል፤ ሀገር ከጥፋት ትድናለች፤ የህዝቦች አንድነትና ሰላምም ይረጋገጣል።
Exit mobile version