አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጤና አገልግሎት ጥራት፣ ተደራሽነትና ፍትሃዊነትን ማረጋገጥ ያስቻሉ የሪፎርም ስራዎች በላቀ ቁርጠኝነትና ቅንጅት ተተግብረዋል አሉ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፡፡
የጤና ሚኒስቴር፣ የክልልና የከተማ መስተዳድሮች ጤና ቢሮዎች የጋራ መድረክ በባህር ዳር እየተካሄደ ነው፡፡
ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የጤናውን ዘርፍ የማዘመንና ለማህበረሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት በማስፋት ረገድ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።
ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመከላከል፣ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ከማሳደግ ባሻገር የህክምና ግብአት በማሟላት አክሞ በማዳን ረገድ ውጤት ተመዝግቧል ነው ያሉት፡፡
በ2018 በጀት ዓመት ዘላቂ የጤና ልማት ግቦችን ታሳቢ በማድረግ የአገልግሎት ጥራት፣ ተደራሽነትና ፍትሃዊነትን ማረጋገጥ ያስቻሉ የዲጂታላይዜሽን እና የሪፎርም ስራዎች በላቀ ቁርጠኝነትና ቅንጅት መተግበራቸውን አንስተዋል፡፡
የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካትና የጤና ቱሪዝምን በተሳካ ሁኔታ እውን ለማድረግ በሰው ሀብት ልማት ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግስቱ በበኩላቸው፥ በክልሉ ችግሮችን በመቋቋም የማህበረሰቡን የጤና ፍላጎት መሰረት ያደረገ ውጤታማ ስራ ተሰርቷል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 11 ሆስፒታሎችን ግንባታቸው በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ማዘጋጀት እንደተቻለ ጠቅሰው፥ በ13 ሆስፒታሎች የሲቲስካን መሳሪያ መሟላቱን ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ ምክክር እየተደረገ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

