አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተጠናቀቀው 2018 በጀት ዓመት በሁሉም የምርት ወቅቶች ከተለያዩ ሰብሎች 160 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ኩንታል ምርት ተገኝቷል፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ጉባዔ በወልቂጤ ከተማ እየተካሄደ ነው ፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ በዓመቱ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የሕዝቡን ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተደረገው ጥረት ውጤታማ ነው፡፡
በሁሉም የምርት ወቅቶች ከ1 ነጥብ 25 ሚሊየን ሔክታር በላይ መሬት በማልማት ከ160 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ኩንታል ምርት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡
በምርት ዘመኑ በበጋ መስኖ ልማት ከ37 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ኩንታል ምርት መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡
የሕዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች በመመለስ ረገድ ጉልህ ድርሻ ያላቸው ቁልፍ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመው÷ የሰላም ግንባታ ሥራን ከማጽናት ጎን ለጎን ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት መሰራቱንም አስረድተዋል፡፡
የኮደርስ ስልጠናና የፋይዳ ምዝገባን ጨምሮ የመሶብ አገልግሎት፣ ገቢ፣ ሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ግብርና፣ የከተማና የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራዎች በልዩ ትኩረት እንዲመሩ ተደርገዋል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በክልሉ የዘመናት ችግር የሆነውን እንግልት ለመፍታት የሚያስችል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን እውን ለማድረግ በተከናወነ ሥራ እስካሁን ሰባት ማዕከላት ሥራ ጀምረዋል ብለዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ የክልሉ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ የተሳተፈበት ፍጹም ሰላማዊ፣ ፍትኃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ መቻሉንም አስታውሰዋል፡፡

