Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በጥራት ማጠናቀቅ የመደመር መንግሥት ባህልና መገለጫ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን

 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአቪዬሽን መሠረተ ልማት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና ምሰሶ ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ ዛሬ የተመረቀው የባሕር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲስ የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል የአየር መንገዳችን ደማቅ የስኬት ጉዞ ማሳያ ነው ብለዋል።

ይህ ዘመናዊ ተርሚናል ለባሕር ዳርና ለአካባቢው ፈርጀ ብዙ ኢኮኖሚያው ፋይዳ ያለው ከመሆኑም በላይ ከተማዋን ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቀጥሎ 2ኛ ትልቅ የዓለም አቀፍ አቪዬሽን ማዕከልነት ሚና እንዲኖራት ያስችላል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ላይ ብቻ ሳይሆን የላቀ ጥራትን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

ከፍተኛ የማስተናገድ አቅም እንዲኖረው ተደርጎ የተገነባው ይህ ደረጃውን የጠበቀ ተርሚናል ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ሃብቶችን ለመጎብኘት የሚመጡ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን በቀጥታና በምቾት ለማስተናገድ በዕጅጉ እንደሚረዳ ጠቅሰዋል፡፡

የንግድና የኢንቨስትመንት ፍሰቱን በመጨመር ምርቶችን በፍጥነት ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ፣ በአቪዬሽን፣ በሆቴልና በትራንስፖርት ዘርፎች ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚያስችል አንስተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ባሕር ዳርን የዓለም አቀፍ ስብሰባዎችና ሁነቶች ማዕከል ለማድረግ ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጥር ነው የገለጹት፡፡

ፕሮጀክቶችን አቅዶ መጀመር፣ በጥራት ፈጽሞ ለሕዝብ አገልግሎት ማብቃት የመደመር መንግሥት ባህልና መገለጫ ነው፤ ይህ የትጋትና የመፈጸም ጉዟችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የውበት፣ የልምላሜና የፀዳል ተምሳሌት የሆነችው ውቧ ባሕር ዳርና የአካባቢው ማህበረሰብ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በመልዕክታቸው፡፡

Exit mobile version