አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከተመረቀ ወዲህ በዓባይ ውኃ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ዙሪያ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተ ቢሆንም ግብፅ የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን መነሻ በማድረግ የምታንጸባርቀው ‘ብቻዬን ልጠቀም’ የሚለው አቋሟ አሁንም ድረስ ቀጥሏል።
በአሜሪካ የፍሎሪዳ የውኃ ሀብት ተመራማሪና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዓለም አቀፍ የምሁራን ጥምረት አባል የሆኑት ጥሩሰው አሰፋ (ዶ/ር) ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቅይታ፤ በዓባይ ተፋሰስ ዙሪያ ለሚነሱ ጥያቄዎች ዘላቂ መፍትሔ የሚገኘው በሳይንሳዊ መረጃ፣ በመተማመንና በፍትሃዊ ትብብር መሆኑን ይናገራሉ።
እንደ ተመራማሪው ገለጻ፤ በፈረንጆቹ 2024 ወደ ሕጋዊ የሥራ ማዕቀፍ የተሸጋገረው የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን የሁሉንም የተፋሰስ ሀገራት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ጠንካራ አቋም ነው።
ሆኖም ግብጽ በተለያዩ የማደናቀፍ አካሄዶችና ተጽዕኖዎች ተቋሙ በሙሉ አቅሙ እንዳይሠራ እንቅፋት ለመፍጠር እየጣረች ትገኛለች።
ግብፅ አሁንም በቅኝ ግዛት ዘመን ውሎች ላይ በመመሥረት ውኃውን ሙሉ በሙሉ ብቻዋን የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያ ውኃውን ለኃይል ማመንጫ ብቻ እንድትጠቀምና ሙሉ በሙሉ ወደ ታች እንድትለቅ የምታደርገው ጫናም የ21ኛው ክፍለ ዘመን እውነታን ያላገናዘበና የትም የማያደርስ አካሄድ መሆኑን ጥሩሰው (ዶ/ር) ይገልጻሉ።
በሌላ በኩል የግድቦች የውሃ መጠን መቀነስ ጋር ተያይዞ የሚነሱት ሥጋቶች መሠረት የሌላቸው መሆናቸው በሳይንሳዊ መረጃዎች ተረጋግጧል ይላሉ።
ለአብነትም ከሕዳሴው ግድብ በታች የሚገኘው የሮዛሪስ ግድብ ኢትዮጵያ በወር የምትለቀው ውኃ ብቻ የሚሞላው መሆኑን ያስረዳሉ።
በተጨማሪም የግብፁ የአስዋን ሐይቅ የውኃ መጠን በአሁኑ ወቅት ከባሕር ጠለል በላይ እስከ 178 ሜትር ደርሶ ሙሉ በመሆኑ የግብጽ የውኃ እጥረት ጩኸት ከሳይንሳዊ እውነታ ይልቅ ፖለቲካዊ መነሻ ያለው መሆኑን ያሳያል።
ኢትዮጵያ የመረጃ ልውውጥንና የጋራ ሥራን ብትጠይቅም ግብፅ ግን የራሷን መረጃ ሳትሰጥ የኢትዮጵያን ብቻ ለመቀበል መፈለጓ ትልቅ ማደናቀፊያ ሆኗል።
ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊየን በላይ ለሚሆነው ሕዝቧ ዘላቂ የምግብና የመጠጥ ውኃ ዋስትና ለማረጋገጥ ከዓባይ ውኃ ለልማትና ለእርሻ መጠቀም ግዴታዋ ነው።
ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በላይ ባሉት ገባሮች ላይ ሁለገብ ፕሮጀክቶችን በመገንባት የዝናብ ጥገኝነትንና የድርቅ አደጋን መከላከልን እንደሚያካትት ተመራማሪው ያብራራሉ።
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ቢኖርም ሳይንሳዊ እውነታዎችን በመቀበልና የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ከላይኞቹ ጋር በጋራ መሥራት ብቸኛውና አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ባለሙያው አጽንኦት ሰጥተውበታል።
ግብጽ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን በመግፋት ‘እኔ ብቻ ውኃውን እንደፈለግሁ ላድርገው’ ማለቷ በዚህ ዘመን ተቀባይነት የሌለው እሳቤ ነው።
ግብጽ የውኃ እጥረት ያጋጥመኛል በሚል በተደጋጋሚ ክስ ብታቀርብም እውነታው ከፍተኛ መጠን ያለው ውኃ ወደ በረሃ መልቀቋና ማባከኗ እንደሆነ ግንዛቤ ሊያገኝ ይገባል።
በዮናስ ጌትነት

