Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ኤርትራን ጨምሮ የቀጣናው ሀገራት ይጠቀማሉ – ኤርትራዊው የማህበረሰብ አንቂ ኢዩኤል ዮሐንስ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ኤርትራን ጨምሮ የቀጣናው ሀገራት ይጠቀማሉ አለ ኤርትራዊው የማህበረሰብ አንቂ ኢዩኤል ዮሐንስ።
ኢዩኤል ዮሐንስ በኤርትራ ዴሞክራሲና ፍትህ እንዲሰፍን የሚሰራ ሰማያዊ ማዕበል የተሰኘ ተቋም መስራች ሲሆን፤ ተቋሙ የኤርትራ ህዝብ የሚፈልገው ሰላም እና ልማት እንዲረጋገጥ በውጭ ሀገራት ከሚገኙ ትውልደ ኤርትራውያን እና ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር እየሰራ ይገኛል።
ከፋና ዲጂታል ጋር ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ቆይታ የነበረው ኢዩኤል ዮሐንስ፤ ኢትዮጵያ ያነሳችው የባሕር በር ጥያቄ የቀጣናውን ሀገራት ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የሚያስችል በመሆኑ ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ በትብብር እንሰራለን ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ ማግኘት በዋነኛነት ኤርትራን ተጠቃሚ ያደርጋል ብሏል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት የቀጣናውን ሰላምና ልማት በማረጋገጥ ረገድ የሚኖረውን አስተዋጽዎም አብራርቷል፡፡
በተለይም በአምባገነን ስርዓት አገዛዝ ስር ለሚገኘውና ልማት ለናፈቀው የኤርትራ ህዝብ እጅግ ጠቃሚ ነው ሲል ገልጿል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት የንግድ ትስስርን በማጠናከር እና ኢኮኖሚን በማነቃቃት ኤርትራን ይበልጥ ተጠቃሚ ያደርጋታል ብሏል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ ያነሳችውን ጥያቄ ለመመለስ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጾ፤ የባሕር በር ጥያቄውን የኤርትራ ህዝብ እንደሚደግፈው አብራርቷል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት ስትሆን በሁለቱ ሀገራት መካከል የድንበር ተሻጋሪ ንግድ እና የሰዎች እንቅስቃሴ ይጨምራል፤ ይህም በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች መካከል ያለውን ማህበራዊ መቀራረብ እንደሚያጠናክር ኤርትራዊው የማህበረሰብ አንቂ ኢዩኤል ዮሐንስ ተናግሯል፡፡
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ህዝቦች በጋራ መስራት፣ የቀይ ባሕር መስመርን ከባሕር ላይ ወንበዴዎች፣ ከሽብርተኝነት እና ከህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በጋራ ለመጠበቅ የሚያስችል ጠንካራ ግንባር መፍጠር ያስችላልም ብሏል።
በምሕረት ደምሴ
Exit mobile version