አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዳያስፖራው በሀገሩ ጉዳይ ላይ የመገለል ሳይሆን የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው አድርጓል አሉ የምክክሩ ተሳታፊ ዳያስፖራዎች።
ተመካካሪ ዳያስፖራዎቹ ምክክሩ በልዩነት ውስጥ አንድነትን በማምጣት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግራት ተናግረዋል።
እንዲሁም ሀገርን በመጥላትና ውጭ ሆነው ጸረ ሀገር ሀሳብ በሚወረውሩ ጥቂት ጽንፈኛ አካላት ከ10 ሚሊየን በላይ የሆነውና እንደ ሻማ እየቀለጠ ቤተሰቡንና ሀገሩን የሚደግፈው ሰፊው ዳያስፖራ ሊወከል እንደማይችል አስገንዝበዋል።
ከዩናይትድ አረብ ኤምሬቶች የመጡት ተመካካሪ ፎዚያ ሁሴን ለፋና ዲጂታ እንዳሉት፤ የትጥቅ ትግል እና ጽንፈኝነት ለሀገር መፍትሄ አያመጣም።
የምክክር ሂደቱ ዳያስፖራው በሀገሩ ጉዳይ ላይ የመገለል ሳይሆን የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው አድርጓል ብለዋል።
ሁሉም ወገን በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ቀጥተኛ የሀሳብ እና የልምድ ልውውጥ ማድረጋቸው ልዩና የተሳካ አጋጣሚ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ሌላኛው ከካናዳ ቶሮንቶ የመጡት ተመካካሪ አቶ ሳምሶን ፀጋዬ በበኩላቸው፤ የተለያዩ ብሔር፣ ሃይማኖት እና አስተሳሰብ ያላቸው ከ4 ሺህ በላይ ዜጎች በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ለውይይት መቀመጣቸው እንዳስደነቃቸው ተናግረዋል።
ጠመንጃ እና ትችት መቼም ቢሆን መፍትሄ ሆኖ አያውቅም ያሉት አቶ ሳምሶን፤ ጠንካራ አንድነት ለመፍጠር የግድ አንድ ዓይነት መሆን አያስፈልግም ብለዋል።
የተለያዩ ሰዎች ለአንድ ዓላማ ሲሰባሰቡ ጠንካራ አንድነት መፍጠር እንደሚችሉ አስረድተዋል።
በጦር መሳሪያ አማራጭ ሀገራዊ አንድነትን ማምጣት እንደማይቻል በተደጋጋሚ መታየቱን አስታውሰው፤ ያልተሞከረው የውይይት ባህል ተስፋ ሰጪ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቁመዋል።
ተመካካሪ ዳያስፖራዎቹ አብዛኛው ዳያስፖራ ሀገሩን በልማትም ሆነ በዘላቂ ሰላም ግንባታ ለመደገፍ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው አመልክተዋል።
የምክክር ሂደቱ ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዳ የውይይት መድረክ መፍጠሩ ተሳትፏቸውን እንደሚያጎላው አመልክተዋል።
በሶስና አለማየሁ

