Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሕገ ወጡ ህወሓትን የጦርነት ቅስቀሳና አፈና ልንታገለው ይገባል – ከቡድኑ አፈና ሸሽተው የመጡ ወጣቶች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕገ ወጡ ህወሓትን የጦርነት ቅስቀሳና አፈና ልንታገለው ይገባል አሉ ከቡድኑ ግፍና አፈና ሸሽተው የመጡ የትግራይ ክልል ተወላጅ ወጣቶች፡፡

ወጣቶቹ ÷ የታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪ የሆነውን ሕገ ወጡን የሕወሓት ቡድን የጦርነት ቅስቀሳና አፈና የትግራይ ሕዝብና ወጣቶች አጥብቀው ሊቃወሙትና ሊታገሉት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሕገ ወጡ የሕወሓት ቡድን በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመቀናጀት የትግራይ ወጣቶችን ለጦርነት በግዳጅ እያፈሰና ወደ ሱዳን በመሸጥ አስከፊ ግፍ እየፈጸመ ይገኛል።

በርካታ ወጣቶችም ይህን ግፍ በመስጋት አካባቢያቸውን ጥለው እየሸሹ ይገኛሉ።

ወጣት ገብረኪሮስ ሕሉፍ ÷ ሕገ-ወጡ ቡድን እየፈጸመ ያለው የጦርነት ጉሰማና ግፍ በፈጸመው ወንጀል ላለመጠየቅ የሚያደርገው ጥረት መሆኑን ተናግሯል።

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የትግራይ ሕዝብን ፍላጎት ለመመለስ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስታውሶ ÷ የፌዴራል መንግሥትም በስምምነቱ የተቀመጡ ጉዳዮችን ሲፈጽም መቆየቱን አንስቷል።

በተቃራኒው ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን ግን ስምምንቱን በመጣስ ለትግራይ ሕዝብ ጥቅም ምንም ዓይነት ደንታ እንደሌለው በተግባር አሳይቷል ነው ያለው።

የትግራይ ሕዝብ የሚሻው ሰላም ቢሆንም፣ ቡድኑ ከሕዝቡ ፍላጎት ውጭ ወጣቶችን በግዳጅ እያፈሰና ጦርነት እየቀሰቀሰ ነው፤ይህም የቡድኑን ውድቀትና በሕዝቡ ዘንድ ቅቡልነት ማጣቱን ያመላክታል ብሏል።

ሕገ ወጥ ቡድኑ ከሻዕቢያና ከሌሎች ተላላኪ ሃይሎች ጋር በመሆን ጦርነት በመቀስቀስ የትግራይ ሕዝብን ለከፋ ችግር ለመዳረግ እየተንቀሳቀስ መሆኑን የሚናገረው ወጣት ኪሮስ፤ በመሆኑም ይህን ሕገ-ወጥ ቡድን አምርረን ልንታገለው ይገባል ነው ያለው።

ወጣት ፀጋልዑል በርሄ በበኩሉ÷ የትግራይ ሕዝብ ሕገ ወጡ ቡድንን ጦርነትና ውጊያ ይበቃናል በሚል አጥብቆ እየተቃወመው እንደሚገኝ ተናግሯል።

ሕገ-ወጥ ቡድኑ የሚቃዎሙትን ወጣቶች ብቻ ሳይሆን ልጆቻችንን ለምንድን ነው የምትወስዱት ብለው ጥያቄ እያነሱ ያሉ እናቶች ላይ ሳይቀር ግፍ እየፈጸመ እንደሚገኝ ለኢዜአ ገልጿል፡፡

የሕገ ወጡ ቡድን አመራሮች እኛ ካልገዛንና ካልዘረፍን ወጣቱና ሕዝቡ አይኖርም በሚል በተለመደው እኩይ ተግባራቸው መቀጠላቸው የመጨረሻ ውድቀታቸውን ያሳያል ፤ እኛ ወጣቶች በሕገ ወጥ ቡድኑ ላይ የጀመርነውን ተቃውሞና ትግል አጠናክረን መቀጠል አለብን ሲልም ጥሪ አቅርቧል።

Exit mobile version