Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የ2019 በጀት 67 ቢሊየን ብር ሆኖ ጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ለ2019 በጀት ዓመት 67 ቢሊየን ብር በጀት አጽድቋል፡፡

የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ጉባኤ ሁለተኛ ቀን ውሎ ቀጥሎ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በምክር ቤቱ የፕላን፣ መሰረተ ልማትና የመንግሥት ሀብት ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ታመነ ገብሬ የ2019 በጀት አመት ረቂቅ በጀትን በዝርዝር አቅርበዋል።

ምክር ቤቱ በቀረበለት ረቂቅ በጀት ላይ ከተወያየ በኋላ ለ2019 በጀት ዓመት 67 ቢሊየን ብር በጀት አጽድቋል፡፡

ከዚህም ውስጥ ከ31 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ከፌደራል መንግሥት ግምጃ ቤት፣ ከውጭ እርዳታና የዘላቂ ልማት ግቦች የሚሸፈን መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አስረድተዋል፡፡

ከ35 ቢሊየን ብር በላይ በክልሉ ከመደበኛ ገቢ፣ ከመስሪያ ቤቶች የውስጥ ገቢ፣ ከጤና ተቋማት ገቢ፣ ከማዘጋጃ ቤትና ከትምህርት ቤቶች ገቢ ይሸፈናል ነው ያሉት፡፡

የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዘይቱና ኢብራሂም በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ባለፉት ሶስት ዓመታት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት ተሰርቷል፡፡

የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በፍጥነት ማጠናቀቅ በተደረገ ጥረት ለዘመናት ግንባታቸው የተጓተቱ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁና አዳዲስ ፕሮጀክቶች ተገንብተው አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን አንስተዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በክልሉ ምክር ቤት እየጸደቀ ያለው በጀት በአማካይ የ23 በመቶ እድገት ማሳየቱን ኃላፊዋ በማብራሪያቸው አመላክተዋል።

Exit mobile version