Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጽምዶ የአምባገነኑ የኤርትራ መንግሥት መጠቀሚያ መሳሪያ ነው – ኤርትራዊው የማህበረሰብ አንቂ ኢዩኤል ዮሐንስ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጽምዶ የአምባገነኑ የኤርትራ መንግስት መጠቀሚያ መሳሪያ ነው አለ ኤርትራዊው የማህበረሰብ አንቂ ኢዩኤል ዮሐንስ።
ሰማያዊ ማዕበል የተሰኘ ዴሞክራሲና ፍትህ በኤርትራ እንዲሰፍን የሚሰራ ተቋም መስራች የሆነው ኢዩኤል ዮሐንስ ከፋና ዲጂታል ጋር ባደረገው ቆይታ፤ ህገ ወጡ የህወሀት ቡድን ያደራጀው ጽምዶ የተሰኘው ጥምረት የስልጣን ጥመኞችን ጥቅም ማስጠበቂያ ነው ብሏል።
ስብስቡ የህዝብ ፍላጎትና ጥቅም የሚያስጠብቅ ሳይሆን፣ በተቃራኒው የህዝብን መከራ የሚያራዝም እና ልማትን የሚያጠፋ የጦርነት ህብረት ነው ሲል ገልጿል።
የአጥፊ ሃይሎች ስብስብ የሆነው ጽምዶ ጥምረቱን በወታደራዊ፣ በፖለቲካዊ እንዲሁም በቴክኒክ ረገድ የሚደግፈውና የሚመራው አምባገነኑ የኤርትራ መንግሥት መሆኑ ግልጽ መሆኑን አብራርቷል።
የስብስቡ ዓላማ ጸረ-ሰላም፣ ጸረ-ልማት እና ጸረ-ዴሞክራሲ በሆነ መንገድ በአምባገነንነት ህዝብን ለሚገዛው የሻዕቢያ አስተዳደር ስልጣን ዕድሜ ማራዘሚያ መሳሪያነት ማዋል እንደሆነ አብራርቷል።
በአሁን ሰዓት የኤርትራም ይሁን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገው ሰላም እንደሆነ ያነሳው የማህበረሰብ አንቂ ኢዩኤል ዮሐንስ፤ በሻዕቢያ ሴራ የመጣው ጽምዶ የአፍሪካ ቀንድን ለማመስና የግጭት ቀጠና ለማድረግ ያለመ የጥፋት ስብስብ መሆኑን አስገንዝቧል፡፡
ጥምረቱ ለሻዕቢያ እና ለሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን ጥቂት አመራሮች የሥልጣን ከለላ የሚሰጥ እንጂ ለሕዝብ የቆመ አለመሆነኑን ገልጾ፤ ስብስቡ የህዝቡን ይሁንታ ፈፅሞ አላገኘም ብሏል፡፡
በጽምዶ ዙሪያ የተሰባሰቡ ኃይሎች ለሻዕቢያ አጀንዳ ፈጻሚና ተላላኪ በመሆን የራሳቸውን ሕዝብ ለጥፋት አሳልፈው እየሰጡ መሆኑን አመልክቷል።
የፌደራል መንግሥት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን እያደረገ መሆኑን አስታውሶ፤ ለህዝቡ የሚያስብ ማንኛውም አካል የሰላም ዕድልን ሊጠቀም ይገባል ነው ያለው።
በምሕረት ደምሴ
Exit mobile version