Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጠንካራ ሰራዊት፤ ጽኑ ሀገር

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሰራዊት የሀገርን ሉዓላዊነት፣ የህዝብን ደህንነትና ድንበርን በአስተማማኝነት በመጠበቅ ረገድ አንፀባራቂ ታሪክ ያለው የሕዝብ ተቋም ነው።
ባለፉት ዓመታት በመደመር መንግሥት ሰራዊቱን ዘመኑን የሚመጥን የቴክኖሎጂ ባለቤት ለማድረግ በተካሄደው አጠቃላይ የመዋቅር፣ የሰው ኃይልና የትጥቅ ሪፎርም ተቋሙን ወደ አዲስ የስኬትና የጥንካሬ ማዕዘን ላይ አድርሶታል::
ሰራዊቱ የማንኛውም ፖለቲካ ድርጅት መሳሪያ ሳይሆን የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና የህገመንግሥቱ ዘብ ብቻ እንዲሆን በከፍተኛ ሁኔታ ተሰርቷል።
በሰላም ማስከበር ስራዎች የሕዝብን የደህንነት ስጋቶች በመቀልበስ ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን ያረጋገጠ ምላሽ በመስጠት ጠንካራ አመኔታ አዝልቋል።
የመደመር መንግሥት የሪፎርም ስራዎች ሰራዊቱን በሰው ኃይል ግንባታ ብቻ ሳይሆን በቴክኖሎጂና በዘመናዊ ትጥቅ የበላይነትን እንዲላበስ አድርጎታል።
የአየር ሀይል የውጊያና የመረጃ ሰብሳቢ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ወይም ድሮኖችን፣ የላቁ ተዋጊ አውሮፕላኖችንና የራዳር ስርአቶችን በመታጠቅ የኢትዮጵያን የአየር ክልል የመጠበቅና ስጋቶች ሲፈጠሩ በፍጥነት ምላሽ የመስጠት አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጓል።
ከበርካታ ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል እንደ አዲስ ተቋቁሞ በዘመናዊ ስልጠና እና መዋቅር እንዲደራጅ መደረጉ በስራቴጂያዊው የቀይ ባህር ቀጣና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ትልቅ መሰረት የሚጥል ርምጃ ነው።
በዘመናዊ ውጊያ የሳይበር ጥቃቶችን የመከላከልና የጠላትን የመረጃ መዋቅር የማስወገድ አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ተገንብቷል።
የሰራዊቱ የሰው ሀይል መዋቅር ወቅታዊውን የዓለም አቀፍና የቀጣናዊ ስጋቶች ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ እንደገና እንዲደራጅ ተደርጓል።
በከፍተኛ የውጊያ ጥበብና አካላዊ ብቃት የሰለጠኑ አዳዲስ የኮማንዶ፣ የአየር ወለድ እና የልዩ ዘመቻ ክፍሎች ተመስርተዋል።
እነዚህ ክፍሎች በየትኛውም የመሬት አቀማመጥ እና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በብቃት ተልዕኮ የመፈጸም አቅማቸው ከፍተኛ ነው።
ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በወታደራዊ ሳይንስ፣ በስትራቴያዊ አመራርና በዘመናዊ ታክቲክ የዳበረ እውቀት እንዲኖራቸው በእውቀትና በክህሎት ብቁ ተደርገዋል።
የሀገር ውስጥ የመከላከያ ኢንዱስትሪዎች ቀላልና ከባድ ወታደራዊ መሳሪያዎችን፣ ተሽከርካሪዎችን፣ ተተኳሾችንና የሎጂስቲክስ እቃዎችን በሀገር ውስጥ የማምረትና የማደስ አቅማቸውን አሳድገዋል።
ይህ አቅም ሀገሪቱ ለትጥቅ ግዢ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከመቀነሱም በላይ በወታደራዊ ሉዓላዊነት ላይ አስተማማኝነትን ፈጥሯል።
ይህ የሪፎርም ስኬት ሰራዊቱ የኢትዮጵያን የውስጥ ሰላምና የድንበር ሉዓላዊነት ከመጠበቅ ባለፈ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና እንዲሁም በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልእኮዎች አስተማማኝ የሰላምና የመረጋጋት አለኝታ ሆኖ እንዲቀጥል አስችሎታል።
በአጠቃላይ በመደመር መንግሥት የመከላከያ ሁለንተናዊ ሪፎርም የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሰራዊት ከብዛት ባሻገር ጥራት፣ ከባህላዊ ውጊያ ወደ ቴክኖሎጂ መር አቅም፤ እንዲሁም ከወገንተኝነት ወደ ተቋማዊ ገለልተኝነት የተሸጋገረበት የታሪክ እጥፋት ሆኗል።
በመልካም ፈቃዱ
Exit mobile version