ኢትዮጵያ ሲያጋጥሟት የነበሩትን የማክሮ-ኢኮኖሚ፣ መዋቅራዊና ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች በዘላቂነት ለመቅረፍ እና የግሉን ዘርፍ የኢኮኖሚው ዋና ሞተር ለማድረግ ከለውጡ ወዲህ ታላቅ ፖሊሲ ቀርጻ ስትንቀሳቀስ ቆይታለች፡፡
ሀገሪቱ በቀረጸችው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትኩረት ከሰጠቻቸው ዘርፎች መካከል አንደኛው የግንባታውን ዘርፍ ማነቃቃትና ማዘመን ነው፡፡
በዚህም መንግሥት ለዘርፉ ባመቻቸው ምቹ የፖሊሲ ከባቢ ምክንያት፣ ባለፉት ስምንት ዓመታት ብቻ በግንባታ ዘርፍ አበረታች ለውጦች እየተመዘገቡ ይገኛሉ፡፡
በኢትዮጵያ የግንባታ ግብዓት የሚያመርቱ የሀገር ውስጥ ፋብሪካዎችንና ድርጅቶችን ለማበረታታት በርካታ መዋቅራዊ፣ የፋይናንስና የፖሊሲ ማሻሻያ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
በዚህም በመንግሥት የግዥ ሥርዓት ውስጥ የሀገር ውስጥ የኮንስትራክሽን ቁሳቁስ አምራቾች ቅድሚያ እንዲያገኙ የሚደግፉ መመሪያዎች ተቀርፀው ተግባራዊ እየተደረጉ ነው፡፡
ይህም የመንግሥት ግዙፍ የቤትና የመሠረተ ልማት ግንባታዎች የሀገር ውስጥ ሲሚንቶ፣ መስታወት፣ ብረት፣ ሴራሚክስ እና መሰል ሌሎች ግብዓቶችን እንዲጠቀሙ ይገደዳሉ፡፡
ከውጭ የሚገቡ የግንባታ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችል ብሔራዊ ስትራቴጂም ተነድፎ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ይህም የሀገር ውስጥ አምራቾች ሰፊ የገበያ ዕድል እንዲያገኙ አስችሏል፡፡
ለግንባታ ዕቃዎች ማምረቻ የሚሆኑ ጥሬ ዕቃዎችን እና ማሽነሪዎችን ከውጭ ሀገር ሲያስገቡ ከቀረጥ ነፃ ወይም በዝቅተኛ ቀረጥ እንዲያስገቡ እየተደረገ ነው፡፡
በተቃራኒው በሀገር ውስጥ በበቂ ሁኔታ የሚመረቱ ዕቃዎች ከውጭ እንዳይገቡ የጉምሩክ ታሪፍ ተጥሎባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ለኮንስትራክሽን ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ (ለሲሚንቶ፣ ብረታ ብረትና ሴራሚክስ ፋብሪካዎች) ቅድሚያ በመስጠት የረጅም ጊዜና ዝቅተኛ ወለድ ያላቸውን ብድሮች እንዲያቀርቡ ተደርጓል፡፡
ለሀገር ውስጥ የግንባታ ማጠናቀቂያ ዕቃዎች (የመስታወት፣ የሴራሚክስና ማርብል) አምራቾች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የመሬት፣ የኃይል (የመብራት) እና የውሃ አቅርቦት በቅናሽ ዋጋ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፡፡
በተለይ ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት ያላቸው የሲሚንቶና የብረታ ብረት ፋብሪካዎች በምርት ሂደት ወቅት የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እንዳያጋጥማቸው ልዩ መስመሮችና ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ተሰርቷል፡፡
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ የሀገር ውስጥ ምርቶች የዓለም አቀፍ የጥራት መመዘኛዎችን እንዲያሟሉ በሰራው ሥራ የቴክኒክ ድጋፍና የምስክር ወረቀት አሰጣጥ ሥርዓት ተግብሯል፡፡
ይህም ምርቶቹ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ወደ ጎረቤት ሀገራት ጭምር እንዲላኩና የውጪ ምንዛሪ እንዲያስገኙ በር ከፍቷል፡፡
በአጠቃላይ፣ ከለውጡ ወዲህ በስምንት ዓመታት ውስጥ በመደመር መንግሥት በግንባታው ዘርፍ የተሠሩና የተመዘገቡት ስኬቶች ሀገሪቱ በራሷ አቅም መቆም እንድትችል ያደረጉ ሆነዋል፡፡
ይህም የሀገር ውስጥ አምራቾችን በማበረታታት የውጭ ምንዛሪ ጫናን ከመቀነስ ባለፈ፣ የዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚነትን አረጋግጧል፡፡

