Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ምክክሩ ለዘመናት የቆዩ ችግሮችን በመፍታት ጠንካራ ሀገረ መንግሥት መገንባት ያስችላል – ተመካካሪዎች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ የምክክር ጉባዔው ለዘመናት ለዘለቁ ችግሮች መፍትሔ በማበጀት የተሻለች ሀገር ለመገንባት ዕድል የሚፈጥር ነው አሉ ተመካካሪዎች ፡፡

በስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ያተኮረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

በዚህም በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ 4 ሺህ የሕዝብ ወኪሎች በስምንት ዐበይት አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ይገኛሉ።

ተመካካሪዎች እንደገለጹት÷ ምክክሩ ለዘመናት ሲንከባለሉ የቆዩ ችግሮችን በመፍታት ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡

ከተመካካሪዎች መካከል ሰይፈጀማል ሀጂ÷ በምክክሩ በሰከነ መንገድ በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን በመግለጽ ሀገራዊ ምክክሩ ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት ለዘላቂ ሰላም እና ልማት ትልቅ መሰረት ይጥላል ብለዋል፡፡

በሰለጠነው ዓለም ማንኛውም ችግር በጠረጴዛ ዙሪያ እንደሚፈታ ያስገነዘቡት ተመካካሪው÷ አሁን በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ምክክርም የዚህ አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላኛው ተመካካሪ መርዱ ገብረስላሴ በበኩላቸው÷ በየትኛውም ሁኔታ በምክክር የማይፈታ ችግር እንደሌለ አስገንዝበዋል፡፡

በመሆኑም ሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያውያንን አንድነት ይበልጥ በማጠናከር ልማት እና ብልጽግናን እንደሚያመጣ ትልቅ ተስፋ መሰነቃቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።

በተለይም ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተውጣጡ ዜጎች የሚሳተፉበት አካታችነት ያለው መድረክ መሆኑ ለምምክር መድረኩ ልዩ ድምቀት እና ትክክለኛ የሀገራችንን ምስል የሚያሳይ መሆኑን አንስተዋል።

የምክክር መድረኩ አሳታፊነት እጅግ አስደሳች ነው፤ ይህ አካሄድ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን የወደፊት ዕጣ ፋንታ በመወሰን ረገድ እኩል ሚና እንዲኖራቸው የሚያስችል ነው ያሉት ደግሞ ተመካካሪ ገበየሁ ደጎየ ናቸው፡፡

ይህ መድረክ ለዘመናት ለቆዩ አለመግባባቶች ዘላቂ መፍትሔ በመስጠት ሁሉም ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር ምቹ ዕድል እንደሚፈጥር አመልክተዋል፡፡

Exit mobile version