Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ቀጣናውን ከማስተሳሰር እስከ ዓለም አቀፍ ተደማጭነት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአፍሪካ የአንድነት እንቅስቃሴ ውስጥ የአፍሪካውያንን የነጻነት ትግል ከመደገፍ ጀምሮ አህጉራዊ ተቋማትን በመመስረት ታሪካዊ ሚና ተጫውታለች፡፡
የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድና በአህጉሪቱ ያላትን የረጅም ዘመን የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ታሪክ ማዕከል በማድረግ ዓለም አቀፍ ተደማጭነቷን የሚያጎሉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላትን ተሳትፎ ማሳደግ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲንና ከጎረቤት ሀገራት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነትን ማጠናከር ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የጋራ የሰላም፣ የፀጥታና የኢኮኖሚ ጥቅም በማስቀደም ውጤታማ የዲፕሎማሲ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
ከዚህ አንፃር የንግድ፣ የትራንስፖርት፣ የደህንነትና የልማት ትስስርን ለማስፋት የተደረጉ ጥረቶች ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ትስስር የሰጠችውን ትኩረት የሚያመላክቱ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያን ታሪካዊ የባሕር በር ባለቤትነት ጉዳይ ወደ ዲፕሎማሲያዊ አጀንዳ በማምጣት ብዙ ርቀት መጓዝ ተችሏል፡፡
ኢትዮጵያ አጀንዳውን ከንግድና ከኢኮኖሚ ፍላጎት በተጨማሪ ከአካባቢያዊ ትስስር፣ ከሰላምና ከዘላቂ የኢኮኖሚ ትብብር ጋር በማያያዝ ወደ ውይይት ጠረጴዛ አምጥታለች።
የባሕር በር ጉዳይ በአካባቢው ሀገራት መካከል በውይይትና በጋራ ጥቅም መርህ መፍትሄ ሊፈለግለት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ማሳየትም የዲፕሎማሲው ዋና አጀንዳ ሆኗል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንደመሆኗ በአህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ያላትን ሚና በማጠናከር የአፍሪካ ድምፅ በዓለም አቀፍ መድረኮች ጎልቶ እንዲሰማ ተሳትፎዋን አጠናክራ ቀጥላለች።
ይህም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ከአህጉራዊ ጥቅም ጋር በማሰናሰል ለአፍሪካ የጋራ ብልጽግና ቁርጠኛ መሆኗን የሚያመላክት ነው።
ኢትዮጵያ ከቀጣናዊና አህጉራዊ የዲፕሎማሲ ሚናዋ ባሻገር ብሪክስን በአባልነት መቀላቀሏ በመደመር መንግሥት መሪነት የተመዘገበ ሌላኛው የዲፕሎማሲ ስኬት ነው።
ይህ አባልነት ለኢትዮጵያ ከአባል ሀገራቱ ጋር የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ ትብብር ዕድሎችን የሚያሰፋ ነው።
ይህም ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነቷ በአንድ የኃይል ማዕከል ላይ ሳይወሰን በጋራ ጥቅም መርህ ለምትከተለው የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ አቅጣጫ ማሳያ ነው።
ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነቷን ከኢኮኖሚያዊ ጥቅሟ ጋር ለማስተሳሰር ኢንቨስትመንትን ማሳደግ፣ የውጭ ገበያዎችን ማስፋት፣ የቱሪዝም አቅምንና የኢኮኖሚ እድሎችን በማስተዋወቅ ላይ በትኩረት እየሰራች ነው።
በዓለም አቀፍ ጉዳዮች በተለይም አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና እንዲኖራት፤ እንዲሁም በሰላምና ፀጥታ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የምታሰማው አቋም የዲፕሎማሲዋ አካል ሆኗል።
በቅርብ ዓመታት የፈረንሳይ፣ የብራዚል እና የቱርክዬ ፕሬዚዳንቶች፤ የሕንድና የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች በኢትዮጵያ ያደረጓቸው ይፋዊ ጉብኝቶች የኢትዮጵያን አሁናዊ የዲፕሎማሲ ከፍታ የሚያሳይ ነው።
በኃይለማርያም ተገኝ
Exit mobile version