አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን እውነተኛ ጥያቄ ያለው ሳይሆን የውጭ ጠላት መሳሪያ ሆኖ እየሰራ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኦቢኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን በውጭ ጠላቶቻችን ተገዝቶ ኢትዮጵያን በመረበሽ፣ ሰላም በማሳጣት መቀጠል ይፈልጋል ብለዋል፡፡
ይህ ቡድን እኩልነትን መቀበል የማይችል ኃይል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በሀገሪቱ ካሉ ከየትኛውም ብሔር ብሔረሰብ ጋር እኩል መታየት እንደማይፈልግ አንስተዋል፡፡
ይህ ባህሪ አሁንም ሁኔታዎች ከተቀየሩ፣ ዓለም ከተቀየረ ወዲህ አለመቀየሩን ገልጸው÷ አሁንም ከኦሮሚያና አማራ ክልል ካሉ ተላላኪዎች አጋዥነት በቡድኑ መሪነት በመንግሥት ላይ ጦርነት ለመክፈት በግልፅ እየተናገረ ነው ብለዋል።
አሁንም ሰዎቹ ናቸው የሚመሩት። ሌላው ይከተላል። ከሰዎቹ ጋር ትብብር ፈጥረው ለመምራት አይደለም፤ እኩልነት አይደለም፤ እንደ ቁጥራቸው ለመምራት አይደለም፤ ሰዎቹ ይመራሉ ሌሎቹ ይመራሉ ሲሉ አብራርተዋል።
በዚህ መልክ የመጣው ሰው ስልጣን ሳይዝ ካልመራሁ ካለ፣ ስልጣን ሲይዝ ምን ሊያመጣ እንደሚችል ስልጣን ሰጥተን አይተናል፣ እናውቃለን ውጤቱን ነው ያሉት።
የሕገ ወጡ ሕወሓት ቡድን መሪዎች አሁንም እኩልነት አይቀበሉም፤ በዚህ ዘመን እኩልነትን የማይቀበል ደግሞ በጣም ይቸገራል ብለዋል፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
የደርግን መንግሥት አሸንፎ ስልጣን የያዘው በራሱ ሳይሆን በሌሎች ድጋፍ እና እገዛ መሆኑን አስታውሰው÷ አሁንም ተደግፈው የሆነ ነገር ማድረግ የሚችሉ ይመስላቸዋል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
በቴዎድሮስ ሳህለ

