አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች ላይ የተሰማሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመንግሥት ካቢኔ ውስጥ እንዲካተቱ መደረጉን የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋቱን ያረጋገጠ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኦቢኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት÷ ከለውጡ በፊት በነበረው መንግሥት የሕዝቡን ቁጥር መሰረት ያደረገ ፍትሃዊ የሕዝብ ውክልና እና የስልጣን ክፍፍል አልነበረም፡፡
በወቅቱ የነበሩት አራቱ ፓርቲዎች እያንዳንዳቸው ዘጠኝ ሥራ አስፈጻሚዎች እንደነበራቸው ጠቁመው÷ ይህም የሕዝብ ቁጥሩን ያላገናዘበ እና ኢፍትሃዊ አሰራር እንደነበር ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይህ የሆነውም ገዢው ፓርቲ ህወሓት ከሕዝቡ ቁጥር ማነስ የተነሳ ፓርላማ ውስጥ እኩል ድምጽ ስለማይኖረው ውሳኔዎችን የሚወስነው በፓርቲ ስለነበር ነው ብለዋል ፡፡
አሁን ላይ ግን የብልጽግና ሥራ አስፈጻሚ ውክልናው እንደ ሕዝቡ ቁጥር ልዩነት አለው ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ውክልናው የሕዝቡን ቁጥር የድርሻውን ያህል፣ የተሳትፎውን እና ያበርክቶውን ያህል መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
ሆኖም ግን ከዚህ ቀደም ኢፍትሃዊ በሆነ መንገድ እኩል ድምጽ የነበራቸው ዝም ብለው መቀበል ይከብዳቸዋል ፤ ደስተኛ ይሆናሉ ተብሎም አይጠበቅም ነው ያሉት፡፡
በሌላ በኩል ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በርካታ ዜጎች ከእስር እንዲፈቱ መደረጉን ጠቅሰው፤ ይሁን እንጂ አንዳንዶች ከእስር ከተፈቱ በኋላ ወደ ጫካ በመግባት ትናንት በደል ካደረሱባቸው አካላት ጋር በመጣመር ወደ ጥፋት ተልዕኮ መግባታቸውን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሠላማዊ መንገድ ተንቀሳቅሰው የፖለቲካ ሀሳባቸውን በነፃነት ማቅረብና መግለጽ የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቁመዋል።
በተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች ላይ የተሰማሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመንግስት ካቢኔ ውስጥ እንዲካተቱ መደረጉን ጠቅሰው÷ ይህም የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋቱን ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
ከዚህ ባለፈም የሁሉም ዜጋ ሀሳብ በእኩልነት የሚደመጥበትና ዘላቂ መፍትሔ የሚፈለግበት ሀገራዊ ምክክር እየተካሄደ መሆኑን አብራርተዋል።
በአመለወርቅ ደምሰው

