Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኤሌክትሪክ ሃይል ተደራሽነትን ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዲስ ኃይል ማስቀጠያ ክፍያን በዱቤ ለሚከፍሉ ደንበኞች ይጣል የነበረውን ከ3 እስከ 9 በመቶ የሚደርስ የወለድ ክፍያ ሙሉ በሙሉ ማንሳቱን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጌቱ ገረመው (ኢ/ር) እንዳሉት÷ የወለድ ክፍያው መነሳቱ የአዲስ ኤሌክትሪክ ኃይል ማስገባት ፍላጎት ያላቸው ሆነው የማስቀጠያ ክፍያውን በአንድ ጊዜ መክፈል ለማይችሉ ዜጎች አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ያደርጋል።
በቅርቡ ሥራ ላይ በዋለው የአዲስ ቆጣሪ የዱቤ አሰራር ከሰኔ 2018 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ከ19 ሺህ በላይ አዳዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው አሰራሩ የአዲስ ኃይል ማስቀጠያ ክፍያን በአንድ ጊዜ መፈጸም ለማይችሉ ደንበኞች ክፍያውን በተወሰነ ጊዜ ተከፋፍለው እንዲከፍሉ ዕድል ይሰጣል ብለዋል።
ቀደም ሲል የዱቤ ክፍያ ጊዜው እስከ 24 ወራት የሚደርስ እንደሆነ እና ከ6 ወራት በላይ ለሚቆይ ክፍያ ከ3 እስከ 9 በመቶ የሚደርስ ወለድ ይታሰብ እንደነበር አንስተው አሁን ግን ይህ የወለድ ክፍያ ሙሉ በሙሉ መነሳቱን ጠቁመዋል።
የወለድ ክፍያው መነሳቱ የአዲስ ኃይል ማስቀጠያ ክፍያን በአንድ ጊዜ መፈጸም ለማይችሉ ደንበኞች የክፍያ ጫናን የሚያቃልል ውሳኔ እንደሆነ እና ደንበኞችም በዱቤ ክፍያ ሥርዓቱ አማካኝነት አዲስ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስገባት እንደሚችሉ አመልክተዋል።
ውሳኔው ኃይልን ለበለጠ የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ፣ ዜጎች ከኤሌክትሪክ ኃይል የሚገኘውን ጥቅም እንዲያገኙ ለማስቻል እና የደንበኛ ተኮር አገልግሎትን ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።
የዱቤ ክፍያ አሰራሩ የዜጎችን የአንድ ጊዜ የክፍያ ጫና በማቃለል የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ከማስፋፋቱ ባለፈ የአዳዲስ ደንበኞችን ቁጥር ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚህ መሠረት የዱቤ ክፍያ ሥርዓቱን በተሻሻለ አሠራር ማጠናከር እና የወለድ ክፍያን ማንሳት የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን በማስፋፋት በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተቋሙን የቀጣይ ዕቅድ የሚያጠናክር መሆኑን ኢንጂነር ጌቱ ገረመው አጽንኦት ሰጥተዋል።
በ2019 በጀት ዓመት 1 ነጥብ 1 ሚሊየን አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድ መያዙን ገልጸው ዕቅዱ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን በማስፋፋት ቁጥሩ የሚጨምረውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ ከሚከናወኑ ሥራዎች አንዱ መሆኑን አብራርተዋል።
ተቋሙ በ70 ዓመታት ታሪኩ ያገናኛቸው የደንበኞች ቁጥር 5 ነጥብ 88 ሚሊየን ያህል መድረሱን እና በ2018 በጀት ዓመትም 664 ሺህ 505 አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸው አፈጻጸሙ ተቋሙ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን በማስፋፋት ያለውን አቅም የሚያሳይ መሆኑ አስረድተዋል።
Exit mobile version