Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮ ኮደርስ ኢኒሼቲቭ የስኬት ምዕራፍና የወጣት አዝመራው ታደሰ ተነሳሽነት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አዝመራው ታደሰ የ 5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ኢኒሼቲቭ ተመራቂ ወጣት ባለሙያ ነው።
ወጣቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በ5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ኢኒሼቲቭ ዙሪያ ባዘጋጀው የልምድ ልውውጥ መርሐ ግብር ላይ በመገኘት ተሞክሮውን አካፍሏል፡፡
ወጣት አዝመራው በመርሐ ግብሩ ላይ እንዳለው ፥ ይህንን ታላቅ ዕድል በዩኒቨርሲቲ ቆይታው የመጨረሻ ዓመታት ውስጥ በመቀላቀል አስደናቂ የስኬት ምዕራፍ ላይ ደርሷል።
ወጣቱ ኮድ ማድረግን መማር ከጀመረበት ጥረት ተነስቶ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ኮደሮችን የሚያገናኝ ድረ ገጽ ወደ ማበልጸግ መሸጋገር መቻሉንና ዛሬ ደግሞ ፉል ስታክ ድረ ገጽ አልሚ መሆኑን አስረድቷል።
በሰርተፍኬት ብቻ አትወሰኑ የሚለው ወጣት አዝመራው የተማራችሁትን በተግባር በማዋል እና በመለማመድ እውነተኛ ዕድገት ማምጣት ትችላላችሁ ሲል ተናግሯል።
‎በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ሥዩም እንዳሉት ፥ የወጣቶች የቴክኒክና የዲጂታል ክህሎት ብቃት ወሳኝ ሀገራዊ ሀብት ነው፡፡
በዚህ ክረምት የኮደሮችን ቁጥር 7 ሚሊየን ለማድረስ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበውን ጥሪ ተግባራዊነት አረጋግጠዋል።
Exit mobile version