Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በገቢና ንግድ ዘርፎች ላይ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን ለመፍታት በቁርጠኝነት ይሰራል – እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በገቢና ንግድ ሥርዓት ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት አስገዳጅ ሕግ የማስከበር ሥራ ላይ ትኩረት ይደረጋል አሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)፡፡
በክልሉ ሕገ ወጥ ንግድ ቁጥጥር፣ ኑሮ ማረጋጋት እና የታክስ ህግ ተገዢነትን ለማጠናከር ያለመ ምክክር እየተካሄደ ነው፡፡
እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ በገቢና ንግድ ዘርፎች የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን በዘላቂነት ለማስወገድ መወያየትና ለቀጣይ ሥራ ተግባቦት መፍጠር አስፈላጊ ነው፡፡
የታክስ ሕግን በማስከበር ገቢን ለማሳደግ የጋራ ጥረት ይጠይቃል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ÷ የገቢ አሰባሰብ ሒደቱ የክልሉ ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው ገቢ አንጻር አሁንም ቀሪ ስራ እንዳለ አመላክተዋል።
የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት እያደገ ሲሄድ የክልሉን ከተሞች የመሰረተ ልማት ፍላጎት ማሟላት እንደሚያስችል አብራርተዋል።
በየጊዜው እያደገ ለመጣው የሕዝብ የልማት ፍላጎት ምላሽ መስጠት የሚቻለው ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ ሲቻል ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በክልሉ የንግድ ሥርዓቱን መቆጣጠር እና መስመር ማስያዝ ይገባል፤ በሀገሪቱ የሚወጡ ደንቦች እና መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
በንግድ እና ገቢ ዘርፎች እያጋጠመ ያለውን ችግር በመፍታት ረገድ የላቀ ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅም ርዕሰ መስተዳድሩ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
እያጋጠመ ያለውን የዋጋ ንረት በመቆጣጠር በሕብረተሰቡ ላይ የሚያሳድረውን ጫና ለመቀነስ በትኩረት መስራት ይገባል ማለታቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመልክቷል፡፡
Exit mobile version