አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከተሜነትን በአግባቡ ለማስተዳደር፣ ከተሞችንና የዜጎችን አኗኗር ለማዘመን ውጤታማ የከተማ ልማት ስትራቴጂን ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች፡፡
ይህ የከተማ ልማት ስራ ከተሞችን ከውበት ባሻገር የዘላቂ ሀገራዊ ልማት ስትራቴጂ አካል ሆኖ በከፍተኛ ትኩረት እየተተገበረ ይገኛል።
ከተሞችን ከዓለም አቀፍ የዘመናዊ ከተማ እሳቤ ጋር በማጣጣም በሕዝብ አገልግሎት መሠረተ ልማቶች፣ በኮሪደር ልማት፣ በወንዞች ዳርቻ ልማት፣ በአረንጓዴ ስፍራዎች ላይ ሰፋፊ ስራዎች ተሰርተዋል።
በኮሪደር ልማት የተሽከርካሪ መንገዶችን ከማስፋት ባለፈ የእግረኛና የብስክሌት መንገድ እንዲሁም የሕዝብ መዝናኛ ስፍራዎች በጥራት ተገንብተዋል።
አዲስ አበባን ጨምሮ በሀገሪቱ በሚገኙ ከተሞች እየተከናወኑ ያሉ የከተማ ልማት ስራዎች ለኑሮ ምቹ እንዲሁም ለጎብኚዎች ሳቢ ከተሞችን ለመፍጠር የተያዘውን አቅጣጫ ያሳያሉ።
የዘመናዊ ከተሞች ዋነኛ መለኪያዎች ሰዎች በምቾት የሚንቀሳቀሱበት፣ የሚዝናኑበት፣ የሚሠሩበትና የሚኖሩበት ምቹ አካባቢ መፍጠር ነው።
ከእንጦጦ እስከ ቀበና የተከናወነውን የወንዝ ዳር ልማት ስራ ጨምሮ በአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት ዐይን ገላጭ ተግባራት ተከናውነዋል።
ይህ ልማት ቀደም ሲል ለቆሻሻ፣ ለጎርፍና ለጤና አደጋ የተጋለጡ የወንዝ ዳርቻዎችን ወደ አረንጓዴ ስፍራ በመቀየር የአካባቢ ጥበቃንና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን አሰናስሎ ማስኬድ እንደሚቻል ማሳያ ሆነዋል።
ዘመናዊ ከተማ የሚለካው በውብ ገጽታዎች ብቻ አይደለም፤ በሥራ ዕድሎች፣ በንግድ እንቅስቃሴዎች፣ በተቀላጠፈ የትራንስፖርት እንቅስቃሴና በኢንቨስትመንት ምቹነት ጭምር ነው።
በዚህ ረገድ እነዚህ የከተማ ልማት ሥራዎች ከፍተኛ የስራ እድል በመፍጠር፣ በክህሎት ልማትና በእውቀት ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።
በተለይም የኮሪደርና የወንዝ ዳር ልማት፣ የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዲሁም የኮንፈረንስ ማዕከላት ግንባታ የመዲናዋን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት በማጉላት በተለይም በኮንፈረንስ ቱሪዝም ለኢኮኖሚው ከፍተኛ ሚና እያበረከቱ ነው።
ልማቱ ከአዲስ አበባ ባሻገር ወደ ሌሎች ከተሞች እየተስፋፋ ሲሆን፣ ይህም ከተሞችን በተናጠል የሚገነቡ የልማት ማዕከላት ሳይሆኑ በንግድ፣ በቱሪዝም፣ በሎጂስቲክስ፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች እንዲተሳሰሩ ዕድል ይፈጥራል።
የዘመናዊ ከተሞች ግንባታ ቱሪዝምንና ኢንቨስትመንትን የሚስብና የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያጠናክር የልማት መሠረት ነው።
ዘላቂ፣ አረንጓዴ፣ ተደራሽና ለሕዝብ ምቹ ከተሞችን ለመፍጠር እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የዛሬን ችግር ከመፍታት ባሻገር ለነገዋ ኢትዮጵያ የከተማ ምስረታ መሠረት የሚጥሉ ስትራቴጂያዊ ኢንቨስትመንቶች ናቸው።
በአዲስ አበባ የተከናወኑ የቱሪዝም ልማት ፕሮጀክቶች የከተሞችን ቱሪዝም ያነቃቁ ሲሆን፤ ለአብነትም የወዳጅነት ፓርክ ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ ወደ 1 ቢሊየን ብር ገደማ ገቢ አስገኝቷል፡፡
እነዚህ ፕሮጀክቶች ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሥራ ዕድሎችንና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ በጥሩ ሁኔታ የታቀዱ የሕዝብ መገልገያ ሥፍራዎች ለከተማነት ዕድገት አስተዋጽኦ እያበረከቱ ሰዎችን እንዴት ማገናኘት እንደሚችሉ ማረጋገጫ ነው።
በመዲናዋ እና በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች የተገነቡና በመገንባት ላይ የሚገኙ አዳዲስ ቦታዎች እሴት የሚፈጥሩ፣ ዕድሎችን የሚያመቻቹና የኢትዮጵያውያንን ባለቤትነትን የሚያረጋግጡ ማዕከላት መሆናቸውንም ነው የገለጹት።
በኃይለማርያም ተገኝ

